
ባሕር ዳር: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የሦስተኛ ቀን ጉባኤውን እያካሄደ ነው። ምክር ቤቱ በሦስተኛ ቀን ውሎው የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።
የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ዋና ኦዲተር አማረ ብርሃኑ (ዶ.ር) አቅርበዋል።
በክልሉ በኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ የኦዲት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ስጋተ ኦዲት ያለባቸውን መሥሪያ ቤቶች የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት የፋይናንስ እና ሕጋዊነት የኦዲት ሽፋን እንዲያገኙ እንደሚያደርጉም አንስተዋል። የክልሉን የልማት የትኩረት አቅጣጫዎች፣ ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣ የሕዝብ ጥያቄ ያለባቸው ተቋማትን በመለየት የተቋማትን ውጤታማነት በክዋኔ ኦዲት እያረጋገጠ መኾኑን ገልጸዋል። የተቋሙን ነጻነት እና ገለልተኛነት ለማጠናከር እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
በተለያዩ ተቋማት ላይ የኦዲት ሥራ መሥራታቸውንም ገልጸዋል። የፋይናንስ አሥተዳደር ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በተከናወነ የኦዲት ሥራ የሂሳብ አያያዝ ግድፈቶች፣ የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች እና የሕግ ጥሰት የታየባቸው መኖራቸውን ተናግረዋል። የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጥሩ አሠራሮችን እየፈተሹ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ማምከን እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል። የመንግሥት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዲሻሻል ቅንጅታዊ አሠራሮችን እና የመረጃ ልውውጥን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
የኦዲት ግኝቶችን ርምጃ አወሳሰድ እና ማሻሻያ አስተያየቶች ትግበራን ለማጠናከር ድጋፍ እና ክትትልን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል። በክልሉ ኦዲት ተደራጊ ቁጥር መብዛት እና በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የልዩ ኦዲት ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ ለረጅም ጊዜ ሳይሻሻል የቆነው የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት መዋቅራዊ አደረጃጀት ትኩረት ሊያገኝ ይገባል ነው ያሉት።
የምክር ቤት አባላት በጀትን በአግባቡ ለመጠቀም ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል። የኦዲት የማስመለስን አቅም ማሳደግ እና ሃብትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል። ለጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተሩ በተሠሩት ሥራዎች ኦዲት የማስመለስ አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የውስጥ ኦዲተርን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሁሉም አካባቢዎች ላይ በተሟላ መንገድ ሥራ መሥራት አለመቻላቸውንም ተናግረዋል። ምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!