
ደሴ: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አግማስ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ዛሬ በሀርቡ የመጠለያ ካምፕ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት አስጀምሯል።
ፕሮጀክቱም በልብስ ስፌት፣ በብየዳ ሥራ፣ በፍየል ንግድ፣ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዲሁም በእንጀራ እና ዳቦ ቤት ሥራ እንደኾነም ተብራርቷል። ወጣት ዑስማን ሰይድ እና አይሻ አሕመድ ከሦስት ዓመት በፊት ነበር ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የመጡት። ምንም እንኳን የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው እዚህ ቢደርሱም በቋሚነት ሥራ ሳያገኙ እንደቆዩ ያስታውሳሉ።
ነገር ግን አሁን በአግማስ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት በተመቻቸላቸው የሥራ ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውንም ለመለወጥ ዝግጁ መኾናቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል። አግማስ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በ18 የመጠለያ ጣቢያዎች የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን የድርጅቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አብዱሰላም ሽፋው ገልጸዋል።
ዛሬ በሀርቡ መጠለያ ካምፕ ለሚገኙ ወገኖች ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለተፈናቃዮች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። በዚህ ፕሮጀት በቀጥታ 80 ተፈናቃዮች ተጠቃሚ ይኾናሉ ብለዋል አቶ አብዱሰላም። በ12 የመጠለያ ጣቢያዎች ከ16 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውን የተናገሩት የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓሊ ሰይድ ከመንግሥት እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚገኙ ድጋፎችን ለተፈናቃዮች የመደገፍ ሥራ ሢሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።
አግማስ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ያደረገው ድጋፍ በቤተሰብ ደረጃ ከ400 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ለሌሎች አጋር ድርጅቶችም ተፈናቃይ ወገኖች በቋሚነት የሚቋቋሙበትን ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ አሊ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!