የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ አባላት የባሕር ዳር ከተማን የልማት ሥራዎች ተዘዋውረው ተመለከቱ።

53

ባሕር ዳር: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ የልዑካን ቡድን ባሕር ዳርን እየጎበኘ ነው። ቡድኑ በቆይታው የስድስት ወራት አፈጻጸሙን የሚገመግም ይኾናል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣት ክንፍ ኀላፊ አብዱ ድንቁ በጉብኝታቸው ባሕር ዳር ሰላም መኾኗን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። ባሕር ዳር ረጅም ዕድሜ እንዳላት እና አሁን በብልጽግና ልማት ትሩፋት እየለማች መኾኑን አይተናል ብለዋል።

እንዴት ባሕር ዳር ትሄዳላችሁ የሚሉን ነበሩ፤ ነገር ግን በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚወራው ሳይኾን ከተማዋ በሰላም እና በልማት ላይ መኾኗን አይተናል ብለዋል። የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ፈዲላ ቢያ በበኩሏ ባሕር ዳር ከተማ በሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ መኾኑን እንደተመለከተች ገልጻለች።

የኢትዮጵያን ከፍታ ከምናሳይባቸው ውስጥ አንዷ ባሕር ዳር ናት። የኮሪደር ልማት በባሕር ዳር በስፋት እየተሠራ ነው። ይህም ከተማዋ የሚገባትን ደረጃ እንደሚሰጣት ገልጻለች። ባሕር ዳር በተፈጥሮ የታደለች በመኾኗ ትንሽ ተጨምሮበት ማሳደግ ይቻላል። በባሕር ዳር የዓባይን ድልድይ በመገንባት የሕልምን ጉልበት እና ቃልን ወደ ተግባር የመለወጥ ሥራ ያየንበት ነው ብላለች።

ሀገሪቱ በፈተና ውስጥ ኾና ይህንን የመሰለ ልማት መሠራቱ ችግርን ወደ እድል የመለወጥ ማሳያ ነውም ብላለች። በማኅበራዊ ሚዲያ የምንሰማት እና በተግባር የምናያት ባሕር ዳር የተለያዩ ናቸው። የባሕር ዳርን ልማት እና በልማት ላይ መኾን ሌሎችም እየመጡ ቢመለከቱ መልካም ነው ብላለች።

በብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባንግ ኩመዳን ባሕር ዳርን ከረገጥን ጀምሮ ቆይታችን ያማረ ነው። የሚፈጸሙት ልማቶች የሚያስደስቱ ናቸው። የኮሪደር ልማት፣ የዓባይ ድልድይ እና በስታዲየሙ የሚደረገው ልማት የሚስብ ነው።

ወጣት ለልማትም ለጥፋትም ሊውል ይችላል ያለችው አባንግ ያለፉ የወጣቱ የለውጥ ታሪኮችን ጠቅሳ ከለውጥ ማምጣት ውጪ የፖለቲካ ተሳትፎው አነስተኛ እንደነበር ገልጻለች። አሁን በብልጽግና ፓርቲ የወጣቱ ፖለቲካዊ ተሳታፊ ጥሩ መኾኑንም ተናግራለች። በዚህም ወጣቱ ተጠቃሚ እንዲኾን እየሠራን ነው ብላለች።

ልዑካን ቡድኑ በባሕር ዳር ከተማ የተገኘው የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ለመገምገም ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ጌጥ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ!
Next articleበተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውን ለመለወጥ ዝግጁ እንደኾኑ ተፈናቃዮች ተናገሩ።