የኢትዮጵያ ጌጥ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ!

46

ባሕር ዳር: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ደምቃ የምትታይባቸው ጌጥ የኾኑ ተቋማትን በመሪዎቿ ጥረት ሠርታለች። ከእነዚህ ተቋማት መካከል የአፍሪካ ኅብረት ተጠቃሽ ነው። ሁሌም የካቲት ወር ሲመጣ ይህ ተቋም ኢትዮጵያን ያስውባታል። ሥሪቷንም ለዓለም ይገልጣል።

በርካታ አፍሪካውያን በዚህ ወቅት ወደ አንዲት ሀገር ይሰባሰባሉ። ይህች ሀገር ለእነሱ የነጻነት ምልክታቸው ናትና ወደዚች ሀገር ይተምማሉ። ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት መኾኗንም በዚሁ ጊዜ ፍንትው አድርጋ ታሳያለች። ኢትዮጵያ በኅብረት ነገሮችን በመከወን ጥቅሙን ከማንም በላይ ትረዳዋለች።

ለትብብርም ፈር ቀዳጅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ትብብርን አጥብቃ የምትሻው ያኔ አፍሪካን ለመቀራመት ኀያላኑ በዘመቱ ወቅት ብቻዋን ለነጻነት ቆማ ተሟግታለች፡፡ በዚያ ወቅት ኅብረት ቢኖር ምን ያህል ጥቅም እንዳለው መገንዘብ ቀላል ነው። ኅብረት ሲኖርህ ትፈራለህ፣ ትደመጣለህም። ኢትዮጵያ በዚያ ዘመን ተቸግራም ቢኾን መደመጥ የሚችል የአፍሪካን ኅብረት አቁማለች።

በዘመናት መካከል ብቅ ብለው አሻራቸውን አሳርፈው ያለፉ ኢትዮጵያውያን መሪዎች ፖለቲካዊ እሳቤያቸው ልዩነት ቢኖረውም እንኳን ለአፍሪካውያን ኅብረት ያላቸው ዕይታ ግን ከፍ ያለ ነበር፡፡ አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ብዙ ነገር ወርሰዋል፣ እንደ ምሳሌም አድርገው ብዙ ነገሯን ወስደዋል።

ኢትዮጵያውያን መሪዎች በሄዱበት የአፍሪካ ሀገር ሁሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲሄዱ ያስቻላቸው ባለፉት ዘመናት ለአፍሪካ በተከፈለ መስዋዕትነት ነው። አፍሪካውያንም የተደረገላቸው ታላቅ ነገር ዛሬም ድረስ ለኢትዮጵያውያን መሪዎች የሚሰጡት ክብር ከልብ እንዲኾን አድርጎታል፡፡

ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ ኅብረት መመስረት ፊታውራሪ ናቸው። ለዚህውለታቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ አፍሪካውያን መሪዎች ሐውልታቸውን በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ሠርተው አስቀምጠዋል፡፡ በተለያዩ ሀገራትም በስማቸው መንገድን ጨምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች መታሰቢያቸውን ያስቀመጡ በርካታ ሀገራት ናቸው።

አሁን የአፍሪካ ኀብረት 38ኛው ጉባኤ ሊካሄድ ኢትዮጵያ ደግሞ ጉባኤውን ልታስተናግድ ዝግጅቷን ጨርሳለች፡፡ አፍሪካውያንም በዚሁ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ እናት ምድራቸው ለመግባት ምዝገባ አድርገው አሁን ላይ በመግባትም ላይ ይገኛሉ። አፍሪካውያንም ኅብረታቸውን ሊያጠናክሩ፣ ሰላማቸውን ማጽኛ መላ ሊዘይዱ እና ስለ እድገታቸው ለመምከር እየተሰባሰቡም ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በመሪዎቻቸው አማካኝነትም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንግዶችን እየተቀበሉም ይገኛሉ። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም የኅብረቱን ጉባኤ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ በመዘገብ የዚህ ታሪክ አካል ሆኖ ይዘልቃል።

ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኹነቶችን አሠራር ለማሻሻል የቴክኖሎጅ ምዝገባ እያከናወነ መኾኑን የወሳኝ ኹነቶች ምዝገባ አገልግሎት ገለጸ።
Next articleየብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ አባላት የባሕር ዳር ከተማን የልማት ሥራዎች ተዘዋውረው ተመለከቱ።