የኹነቶችን አሠራር ለማሻሻል የቴክኖሎጅ ምዝገባ እያከናወነ መኾኑን የወሳኝ ኹነቶች ምዝገባ አገልግሎት ገለጸ።

40

ባሕር ዳር: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የወሳኝ ኹነቶች ምዝገባ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ማስተዋል አለባቸው እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በወሳኝ ኹነቶች ምዝገባ አገልግሎት ትኩረት ከተሰጣቸው ዋነኛ ሥራዎች ውስጥ የቴክኖሎጅ ተደራሽነት እና አጠቃቀም አንዱ ነው።

በግማሽ ዓመቱ በባሕር ዳር፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በሚገኙ 86 ቀበሌዎች በቴክኖሎጅ የታገዘ የኹነቶች ምዝገባ መካሄዱን ነው የገለጹት። ከሳምንት በኋላ በጎንደር ከተማ የቴክኖሎጅ ምዝገባው እንደሚጀምርም ገልጸዋል። በቴክኖሎጅ ምዝገባ መካሄዱ መረጃውን በፍጥነት ለሚመለከተው አካል በማድረስ ለሚፈለገው አገልግሎት ማዋል ተችሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ የጊዜ፣ የጉልበት እና የገንዘብ ወጭን መቀነስ ተችሏል ብለዋል። የቴክኖሎጅ ምዝገባው በተመሳሳይ ጊዜ በማኑዋል ከተመዘገበው በእጥፍ ብልጫ ማሳየቱንም ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 3 ሺህ 882 ደንበኞች የምስክር ወረቀት ለማመሳከር በተቋሙ መስተናገዳቸውንም የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ 98 በመቶ የሚኾኑት ተገቢውን አገልግሎት አግኝተዋል። ቀሪዎቹ የተጭበረበሩ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን ይዘው በመገኘታቸው በሕግ ቀርበው ርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ሀገራዊ የፓናል ውይይት በቡታጅራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
Next articleየኢትዮጵያ ጌጥ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ!