
አዲስ አበባ: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት “ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ሀገራዊ የፓናል ውይይት እና የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ መድረክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን በቡታጅራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር)፣ የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ.ር) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ.ር)፣ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዳዊት ሀይሶ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መሳፍንት ተፈራን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
በፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዩ በክልሉ ያለውን የዕርቅ እና የሰላም መንገዶች፣ ባሕላዊ እሴቶች፣ የቱሪዝም እና የግብርና ጸጋዎች፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሁም የሰላም ውይይት መድረኮችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ለዕይታ ቀርበዋል። መድረኩ ”ሰላም እና ኢኮኖሚ ስለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደ ሲኾን በግብርና፣ በኢኮኖሚ እና ሰላም ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ “ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘው መድረክ ዋና ዓላማ የሃሳብ እና የማንነት ብዝኅነት በምታስተናግደው ኢትዮጵያ የወል ትርክትን መገንባት ነው ብለዋል። እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ከተፈለገ ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር የመፍታት ባሕልን ማዳበር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
መድረኩ በ2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲኾን “ስለ ኢትዮጵያ” በተሰኘው የጋራ ማንነት እና የወል ትርክት የመገንባት ጉዞም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል። ለአብነትም ለምክክር መድረኩ ጥሩ መደላድልን በመፍጠር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማዳበር፣ የፖለቲካ ክፍፍልን እና ልዩነቶችን በማጥበብ፣ አካታችነትን፣ ወንድማማችነትን እና አብሮነትን በማጎልበት አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል።
ኢፕድ በምዕራፍ አንድ ስለ ኢትዮጵያ መድረኩ በ14 የተለያዩ ከተሞች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እና ምክክር ማካሄዱ ይታወሳል። “ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘው የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት የሁለተኛ ምዕራፍ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዩ እና የፓናል ውይይቱ በቀጣይም በተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!