የደብረ ታቦር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን በ2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።

45

ባሕር ዳር: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የክልል መንግሥት በጀት እየተገነባ ያለው የደብረ ታቦር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በጥሩ ሂደት ላይ እንዳለ የከተማ አሥተዳደሩ ገልጿል። የተሻለ ውጤት ያላቸው ተማሪዎችን በአዳሪ ትምህርት ቤት በማስተማር ሀገርን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው የተገለጸው።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ የትምህርት ቤቱ መገንባት የላቀ ዕውቀት ያላቸውን ተማሪዎች ለይቶ በማብቃት ለሀገርም ኾነ ለክልሉ ተመራማሪ እና ዓለም አቀፍ መስፈርትን የሚያሟሉ ልሂቃንን ለማፍራት ያስችላል ብለዋል። በ12 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው አዳሪ ትምህርት ቤቱ መጋቢት 2016 ዓ.ም ተጀምሮ በ2018 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ታስቦ ነው እየተሠራ ያለው።

በአንድ ጊዜ 720 ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ ተገልጿል። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰለሞን አዳሪ ትምህርት ቤት በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በጀት እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ግንባታው በሁለት ተቋራጮች የሚከናወን ሲኾን አንደኛው 31 ነጥብ 6 በመቶ እና ሁለተኛው ደግሞ 47 ነጥብ 3 በመቶ አፈጻጸም አላቸው።

ልጃቸውን ደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ አንድ ወላጅ በሰጡት አስተያየት የአዳሪ ትምህርት ቤት በአካባቢው ባለመኖሩ ሩቅ ቦታ ለመሄድ እንደተገደዱ ተናግረዋል።

ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በየአካባቢው መኖሩ የተለየ ብቃት ላላቸው ልጆች ጥሩ ዕድል ነው ብለዋል። ወላጆችም የማስተማርን ጥቅም ተረድተው እንዲያስተምሩ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ የተረጋጋች እና ራሷን የምትችል አፍሪካን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ ናት” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next articleበብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አባንግ ኩሙዳን የተመራ ልዑክ በባሕር ዳር ጉብኝት እያደረገ ነው።