
ባሕር ዳር: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ46ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባዔ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ተሳታፊዎች የክብር እራት ግብዣ አድርጓል። በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው የግብዣ ሥነ ስርዓት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) የአዲስ አበባ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በእራት ግብዣ ሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ወደ ዚህ የእራት ግብዣ ስለመጣችሁ ታላቅ ደስታ እና ጥልቅ ክብር አለኝ ብለዋል። ማዕከሉ ሃሳቦች የሚለዋወጡበት ፣ አጋርነት የሚፈጠርበት ፣ ለአሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች የመፍትሔ ሃሳቦች የሚቃኙበት አስፈላጊ የጥበብ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንግዶችን የማስተናገድ ባሕል የአፍሪካ አንድነት (ኅብረት) ድርጅት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ስታሳየው የቆየችው ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ማዕከል ይህን የተከበረ ባሕል የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል። አዲስ አበባን የኮንፈረንሶች፣ የኤግዚቢሽኖች እና የንግድ ዝግጅቶች መዳረሻ እንድትኾን የማድረግ ትልማችንን ዕውን እናደርጋለን ነው ያሉት።
46ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እያጋጠመን ያለውን ፈታኝ ሁኔታ ለማሰላሰል እና እንደ አሕጉር፣ የጀመርነውን የሰላም፣ የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮች ዳር በማድረስ ለዕድገታችን ወሳኝ ሚና መጫወት የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። የተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ፣ በምግብ እራስን የመቻል፣ የመሠረተ ልማት ትስስር እና የፖሊሲ ማጣጣም ሥራዎች ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ አፍሪካውያን ላይ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካውያን የሚለው መርሕ፣ አንድነት እና አጋርነት የአፍሪካውያን እውነተኛ ፍላጎት ኾነው ይቀጥላሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ እየተለወጠ ያለውን የዓለም የጂኦ ፖለቲካ እና ጂኦ ኢኮኖሚ በማጤን የኅብረቱ አባል ሀገራት ለአፍሪካ ሰላም፣ መረጋጋት እና አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ “ኢትዮጵያ የምናስባትን ሰላማዊ፣ የተረጋጋች እና ራሷን የምትችል አፍሪካን እውን ለማድረግ ቁርጠኝነቷን ታስቀጥላለች” ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያጋጠሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን ለመሻገር የባለብዙ ወገን ግንኙነት እንደሚያስፈልጋት አንስተዋል።
ተሳታፊዎች በፓን አፍሪካ ዕሳቤ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን የመፍታት መርኾን በመከተል ተቋማዊ አቅምን ማጎልበት እና የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በእራት ግብዣው ላይ ከቀናት በኋላ አገልግሎታቸውን የሚያጠናቅቁት የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ተገኝተዋል። ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴም ለአበርክቷቸው ምስጋና አቅርበውላቸዋል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!