
የጤና ሚኒስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት ለ1 ሺህ 382 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በ17 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን አስታውቋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ነው፡፡
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ውስጥ አስራ ሦስቱ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 30 ዓመት ያሉ ናቸው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ እስከ 65 ዓመት ያሉ ጎልማሶች እንደሆኑ መረጃው ያመለክታል፡፡ በ24 ሰዓታት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት ውስጥ 15 ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡
በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት 13 ከጂቡቲና ሶማልያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡና በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው፤ ሁለቱ የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው ሴቶች ናቸው፤ አንደኛው በሙያው ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን ቀሪው አንድ ሰው ደግሞ የጉዞ ታሪክ የሌለውና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ያለው ግንኙነት በመጣራት ላይ ያለ ነው፡፡
ባለፉት 24 ሰዓታት ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ከአዲስ አበባ ከኮሮና ቫይረስ ማገገማቸውም ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለ26 ሺህ 517 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎ በ162 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ተረጋግጧል፤ ከእነዚህ ውስጥ 93 አገግመዋል፤ 63 ሰዎች ደግሞ በለይቶ ሕክምና ክትትል ላይ ናቸው።
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዮቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡