“በአፍሪካ ደረጃ ተምሳሌት የሚኾን የግልግል ዳኝነት ማዕከል የግንባታ ሂደት ተጀምሯል” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

47

ባሕር ዳር: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ቀርቧል። የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ፍርድ ቤቶች የዜጎች መብት እና ነጻነት ስለመከበሩ የሚረጋገጥባቸው የመጨረሻ አማራጭ የኾኑ የፍትሕ መድረኮች ናቸው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተከናወኑ ብለው ካነሷቸው አፈጻጸሞች መካከል ዋና ዋናዎቹ:-

👉የፍርድ ቤቱ የመዛግብት እልባት መስጠት የስድስት ወራት ሥራ ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዕድገት አሳይቷል።

👉 በየደረጃው ከቀረቡ 208 ሺህ 455 መዛግብት ውስጥ 161 ሺህ 578 ያህሉ ወይም 77 ነጥብ 51 በመቶዎቹ እልባት አግኝተዋል።

👉 የአሠራር ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ሕግ እና ሥርዓትን ተላልፈው የተገኙ 26 ዳኞች ተቀጥተዋል። 29 ዳኞች ደግሞ ጉዳያቸው በሕግ ተይዟል።

👉 የሥራ ቦታን ለተገልጋዮች ምቹ ለማድረግ በማሰብ 193 ሚሊየን 231 ሺህ ብር ተመድቦ የጠቅላይ ፍርድ ቤት መሥሪያ ቤት በፍጥነት እየታደሰ ነው።

👉 147 ሚሊየን 295 ሺህ ብር ተመድቦ አገልግሎትን የሚያቀላጥፍ የማስፋፊያ ሕንጻ ግንባታ እየተካሄደ ነው።

👉 የክልሉ መንግሥት በበጀተው 530 ሚሊየን ብር ወጭ በተለያዩ ዞኖች ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው፤ የግንባታ አፈጻጸሞችም አብዛኞቹ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የደረሱ ናቸው።

👉 ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ተምሳሌት የሚኾን የግልግል ዳኝነት ማዕከል የግንባታ ሂደት ተጀምሯል። ማዕከሉ ለቀጣይ 50 ዓመታት የግልግል ዳኝነት ማዕከል እና እንደ “ፍትሕ ቱሪዝም” ኾኖ የሚያገለግል ሲኾን በባሕር ዳር ከተማ ለመገንባት ዲዛይኑ አልቋል።

👉 የፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ሥርዓት በቴክኖሎጅ የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ ነው፤ ይህም የተገልጋዮችን ጊዜ እና ወጭ ይቆጥባል፤ እንግልትንም ያስቀራል።

👉የክልሉ መንግሥት በበጀተው 300 ሚሊዮን ብር ወጭ ፍርድ ቤቶችን በዲጂታላይዜሽን የማዘመን ሥራ እየተከናወነ ነው።

👉 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገ የ219 ሚሊዮን ብር ውል በመውሰድ ተገልጋዮች ባሉበት ኾነው አገልግሎት የሚያገኙበት የዲጂታላይዜሽን ሥራ እየተከናወነ ነው።

👉 አለመግባባትን በመፍታት፣ ቂምና ጥላቻን የሚያሽሩ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቶችን ለማጠናከር እየተሠራ ነው፤ በስድስት ወራት ውስጥ 837 ጉዳዮች በአስማሚዎች ቀርበው 483ቱ በስምምነት ተቋጭተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 80 ነጥብ 5 ሚሊዮን ደርሰዋል” ኢትዮ ቴሌኮም
Next articleየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) ከቱኒዚያ እና ሞሮኮ አቻወቻቸው ጋር ተወያዩ።