
አዲስ አበባ: የካቲት 05/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ የኢትዮ ቴሌኮምን የ2017 ዓም የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በሚመለከት ጋዜጣዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ተቋሙ ቀጣይነት ያለው ዕድገትን እንዲያስመዘግብ መሠራቱን ተናግረዋል። በስድስት ወራቱ የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ማሻሻል፣ የአገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራትን ማሳደግ፣ የገቢ ምንጮችን ማበራከት እና ማስፋፋት፣ የፋይናንስ አቅም ማጎልበት፣ የኦፕሬሽን ልህቀት ማምጣት፣ የኔትወርክ አቅምን ማሳደግ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን አቅም ማሳደግ እና አገልግሎቶችን ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደተሠራባቸው ገልጸዋል።
በኩባንያው በግማሽ ዓመቱ በተሠራው ረቂቅ የሂሳብ ሪፖርት መሠረት አጠቃላይ ገቢ 61 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በማስገኘት የዕቅዱን 90 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት መቻሉን አንስተዋል። ከዓለም አቀፍ አገልግሎት የተገኘ ገቢ 64 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማስገባት የዕቅዱን 63 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት መቻሉን ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 3 ነጥብ 24 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች በማፍራት አጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ብዛት 80 ነጥብ 5 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉንም አስታውቀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ግዙፍ ዘመናዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት በመላ ሀገሪቱ በማስፋፋት የደንበኞች ቁጥርን በማሳደግ በሠራው መጠነ ሰፊ ሥራ ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 17ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ በመግለጫው ተገልጿል።
የደንበኞችን የአገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት ለማሳደግ በግማሽ ዓመቱ 202 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል። በሞባይል ኔትዎርክ በተከናወኑ የፕሮጀክት ሥራዎች ተጨማሪ የ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሞባይል ኔትዎርክ አቅም በመገንባት 86 ነጥብ 1 ሚሊዮን የነበረውን የሞባይል ኔትወርክ አቅም ወደ 90 ነጥብ 7 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
67 ተጨማሪ ከተሞች በድምሩ 491 ከተሞች የ4ጂ እንዲሁም 10 ከተሞች የ5ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ መኾን መቻላቸውንም ተናግረዋል።
በግማሽ ዓመቱ በዘጠኝ ክልሎች በሚገኙ በ71 ወረዳዎች 81 የገጠር ሞባይል ኔትዎርክ ጣቢያዎች ተገንብቷል ነው ያሉት። በአጠቃላይ በ12 ክልሎች በሚገኙ 231 ወረዳዎች 295 የኔትዎርክ ጣቢያዎች ተገንብተው 327 ሺህ 290 የሞባይል አቅም መፍጠር መቻሉን ሥራ አሥፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በመልሶ ማስጀመር ሥራ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአፋር ክልሎች በሚገኙ 216 ከተሞች እና ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ 231 የሞባይል ጣቢያዎች በመጠገን እና መልሶ በማቋቋም አገልግሎት ማስጀመር ተችሏልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ራሄል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!