
ባሕር ዳር: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ2017 ዓ.ም የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምን ገምግሟል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) በችግር ውስጥ ኾኖም “በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ “ከ26 ሺህ በላይ የሚኾን የኀብረተሰብ ክፍል በማወያዬት መማር ማስተማሩን ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል።
እንደ ክልል እና እንደ ከተማ አሥተዳደር በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩ 24 ትምህርት ቤቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ተደርጓል ነው ያሉት። ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በተደረገው የአንደኛ እና የሁለተኛ ዙር የተማሪ ምዝገባ የዕቅዱን 92 በመቶ ተከናውኗል ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩም ለትምህርት ቤቶች ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።
በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ፈተናን ያለምንም እንከን ተጠናቅቆ ሁለተኛው ወሰነ ትምህርት መጀመሩንም ተናግረዋል። የ6ኛ፣ 8ኛ እና12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የብሔራዊ ፈተና ውጤት ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ረጂ ድርጅቶችን እና ሰፊውን የኀብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተደረገው ርብርብ አበረታች ነው ያሉት ኀላፊው የተጀመሩ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅም ጥረት መደረጉን አንስተዋል። በዘጌ፣ መሸንቲ እና ጭስ ዓባይ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎችን ለመመለስ ለሦስተኛ ጊዜ የተማሪ ምዝገባ ይካሄዳልም ብለዋል።
ዘግይተው የሚመዘገቡትን ተማሪዎች በልዩ እገዛ ደግፎ ውጤታማ ለማድረግም ይሠራል ነው ያሉት። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የጭስ ዓባይ ፏፏቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር መኮንን አስማማው በጭስ ዓባይ ከተማ የሚገኙት ሦስት ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ ተማሪዎችን እያስተማሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ በ2017 የትምህርት ዘመን 2ሺህ 150 ተማሪዎችን ለማስተማር መታቀዱን ያነሱት ርእሰ መምህሩ በጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ሰላም ወደ ኾኑ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ሄደው እየተማሩ መኾናቸውን አንስተዋል። ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ 450 ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛልም ነው ያሉት። በሦስተኛው የምዝገባ ሂደትም ተማሪዎችን ለመመዝገብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖም ትምህርት ቤቱ እንዳይዘጋ በማድረግ ረገድ የኀብረተሰቡ ድጋፍ እና እገዛ ከፍተኛ እንደነበር ርእሰ መምህሩ ጠቁመዋል። የዲያስፖራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር መለሰ በለጠ በትምህርት ቤቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የመማር ማስተማሩ ከባለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ያሉት ርእሰ መምህሩ አሁን ላይ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የትምህርት አይነቶችን በመምረጥ እገዛ እና ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።
የሪስፔንስ ኢንተርናሽናል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ደመላሽ አላየ የመጀመሪያውን ወሰነ ትምህርት በዕቅዱ መሠረት ማጠናቀቅ ተችሏል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ የወላጆች ድጋፍ ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በሙሉ ለማሳለፍ የካበተ ልምድ ያላቸውን መምህራን በመመደብ ቅዳሜን ጨምሮም በማስተማር ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ ፦ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!