በከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት መርሐግብር ከ123 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ገለጸ።

21

ደሴ: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት መርሐግብር የታቀፉ ዜጎችን የሥራ እንቅስቃሴ ከክልል እና ከ18 ከተሞች የተውጣጡ የሥራ ኀላፊዎች ጎብኝተዋል። በከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት መርሐግብር ውጤታማ መኾናቸውን የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ለጎብኝዎቹ ገልጸዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ አብዱረህማን አሕመድ እና አምሳል አበራ በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች እና በከተማ ግብርና በመሰማራት አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።መርሐግብሩ የሥራ ባሕላቸው እንዲያድግ፣ የቁጠባ ባሕላቸው እንዲዳብር እና ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ እንዲመሩ እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል።

በቀጣይም የተዘጋጀላቸውን ሸድ በመጠቀም ኑሯቸውን የበለጠ ለማሻሻል ሥራቸውን አስፍተው እንደሚሠሩም ተናግረዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እታፈራሁ አሰግደው ዜጎች በአካባቢ ልማት እና በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ለሦስት ዓመታት በመርሐ ግብሩ ታቅፈው ገንዘብ የቆጠቡ ተጠቃሚዎችን በማኅበር በማደራጀት ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የመሥሪያ ሸዶችን በመገንባት እንዲተላለፍላቸው ተደርጓል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ከተማ እና የመሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱሌይማን እሸቱ በክልሉ በ18 ከተሞች እየተተገበረ ያለው የከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት መርሐግብር በርካቶችን በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ123 ሺህ በላይ ዜጎችንም ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በክልሉ በዚህ ዓመት10 ሺህ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በማስመረቅ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ማቋቋሚያ እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።

መርሐግብሩ የከተማ ግብርናን ጨምሮ ሌሎች የሙያ ክህሎቶችን በማሠልጠን ግለሰቦችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ከተሞች ውብ እና ጽዱ እንዲኾኑ በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ዘጋቢ ፦አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ ተልኮዎች በላቀ ደረጃ እንዲሳኩ መሪዎች ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
Next articleዘግይተው የሚመዘገቡ ተማሪዎችን በልዩ እገዛ ውጤታማ ለማድረግ ይሠራል።