
ባሕር ዳር: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ምድሩ ዘምሮላቸዋል፡፡ እረኞች በተራራዎች አዚመውላቸዋል፡፡ ሊቀ መኳሶች በየቦታው ተቀኝተውላቸዋል፡፡ ገዳማውያን መርቀዋቸዋል፡፡ ጠቢባን ተንብየውላቸዋል፡፡ ሕዝብ ሁሉ ስማቸውን እየጠራ አድንቋቸዋል፡፡ ጀግንነት ከኔ በላይ ላሳር ያለው ሁሉ ደንብሮላቸዋል፡፡ በፍርሃት እና በድንጋጤ እጅ ነስቶላቸዋል፡፡ የእናት ምርቃት የደረሰላቸው፣ የገዳማውያኑ ምክር ያበረታቸው፣ ጀግንነት ከደማቸው ጋር የተዋሐደላቸው ገናና ናቸው፡፡
ኢትዮጵያን እስከ መቃብር ድረስ አፍቅረዋል፡፡ ለእርሷ ክብር ሲሉ የመከራ ጽዋን ተቀብለዋል፡፡ ለፍቅሯ ጉልበታቸውን፣ ዘመናቸውን፣ ደስታቸውን፣ ተድላቸውን ሰጥተው አልበቃ ቢላቸው ሕይወታቸውን ሰጥተዋታል፡፡ ጠጅ እና ወይን ሊንቆረቆርበት በተገባ ጉሮሮ ባሩድ ተጎንጭተውላታል፡፡ ኢትዮጵያን እየተገፉም ይወዷታል፡፡ መከራ እየበዛባቸውም ያፈቅሯታል፡፡
በዘመናቸው የማይሞከረውን ሞክረዋል፡፡ አንድነትን መነሻ እና መድረሻቸው አድርገዋል፡፡ የሀገር ፍቅርን በልባቸው ጽላት ላይ ደመቅ አድርገው ጽፈዋል፡፡ አንድነቷን የማይሹትን ሁሉ ቀጥተዋል፡፡ ከክብሯ የሚያወርዷትን አሳፍረዋል፡፡ ሕዝብን የሚበድሉትን አደብ አስገዝተዋል፡፡ የመከፋፈልን ዘመን ፈጽመው፣ የአንድነት መሠረትን ጥለዋል፡፡ አዲስ ብርሃን በምድሯ ላይ ፈንጥቀዋል፡፡ አዲስ የሥልጣኔ ጮራ ለሀገራቸው አሳይተዋል ንጉሠ ነገሥት አጼ ቴዎድሮስ፡፡
አጼ ቴዎድሮስ የአንድነት ምልክት፣ የጀግንነት ተምሳሌት ናቸው፡፡ በጀግንነታቸው ሀገራቸውን አስከብረዋል፡፡ በጀግንነታቸው አንድነትን አጽንተዋል፡፡ በጀግንነታቸው ሀገራቸውን ሠንደቃቸውን ከፍ አድርገው ሰቅለዋል፡፡ የሀገራቸውን ዝና በዓለሙ ሁሉ እንዲናኝ አድርገዋል፡፡ በጀግንነታቸው የሀገራቸውን ከብር ከተራራ አግዝፈዋል፡፡ ስማቸውንም ገናና አድርገው ከመቃብር በላይ አስቀምጠዋል፡፡
በፈጸሙት ጀግንነት፣ ባሳዩት ጽናት፣ እስከ ሞት ድረስ በታመነ የሀገር ፍቅር ስሜት ታሪክ ከፍ አድርጎ ይጠራቸዋል፡፡ ትውልድም ይኮራባቸዋል፡፡ ይመካባቸዋል፡፡ ለሀገር አንድነት የተነሳ ሁሉ እርሳቸውን አርዓያ እና ምሳሌ አድርጎ ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት መከራ በበዛባት፣ ችግር በጸናባት፣ አንድነት በራቃት፣ ጉልበተኛ በበረከተባት፣ የሀገሬው ሰው አይዞህ ባይ ባጣበት ዘመን የተነሱ ናቸው የአንድነት አባት ይባላሉ፡፡
አጼ ቴዎድሮስ አንድነት በሳሳበት፣ ፍቅር በቀዘቀዘበት የተነሱ ለሀገር ክብር የኖሩ፣ ለሀገር ፍቅርም ያለፉ ጀግንነታቸው በአንድ ዘመን ብቻ የማያበቃ ገናና ንጉሥ ናቸው፡፡ አቤ ጉበኛ አጼ ቴዎድሮስን ሲገልጿቸው ለሀገራቸው ተፈጥረው፣ ለሀገራቸው ኑረው፣ ለሀገራቸው ምቾታቸውንም ሕይዎታቸውንም፣ የሠጡ ገናናው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ይሏቸዋል፡፡ በገዛ እጃቸው ሕይወታቸውን ያጠፉት አጼ ቴዎድሮስ የአንድ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ብቻ ንጉሠ ነገሥት አይደሉም፡፡ አጼ ቴዎደሮስ በዘመናቸው የነበረውን ትውልድ በማይበገረው ብርታታቸው እና በድል አድራጊው ሠራዊታቸው ብቻ አሳምነው የራስ ብቻ ፍቅር፣ ድንቁርና፣ ምቀኝነት፣ አመጽ ሳያቋርጡ በአገነፈሏቸው ጠላቶች ሴራ፣ በውጭ ሰዎች ተንኮል፣ ሀገራቸውን በከበባት የጠላት ኀይል፤ በራሳቸውም ብስጩ እና ግትር ጠባይ ምክንያትነት እስከ ወደቁበት ጊዜ ድረስ ከገናናዎቹ የዓለም ንጉሦች እንደ አንዱ በሚያስቆጥር ታላቅነት መርተውታል፡፡ የዛሬውን እና የወደፊቱን የኢትዮጵያ ትውልድም በመንፈስ ይገዙታል ብለዋል አቤ ጉበኛ፡፡
እኒህ ታላቅ እና ጀግና ንጉሥ ሥራ እና መንፈስ አመዛዝነው በዓለም ከነገሡት ሀገራቸውን አፍቃሪዎች ጀግኖች እና ታላላቅ አሥተዳዳሪዎች ከኾኑ ጥቂት ንጉሦች አንዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በቴዎድሮስ አይነት ተነስቶ፣ በቴዎድሮስ አይነት ሠርቶ፣ በቴዎድሮስ አይነት ያለፈ ታላቅ ሰው ቀድሟቸው ያልተፈጠረ፣ ለሀገራቸው የመጀመሪያው እና እርሳቸው ብቻ ሀገራቸውን አፍቃሪ ናቸው ይሏቸዋል አቤ ጉበኛ፡፡ እርግጥ ነው በየዘመኑ ሀገራቸውን የሚወዱ ብዙ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን እየተነሱ ከጊዜው አስተሳሰብ ጋር ሳይጋጩ ከአካባቢያቸው ጋር ተስማምተው ኖረው በሰላም አልፈዋል፡፡ በእርሳቸው ዘመን ግን በኢትዮጵያ ፍቅር የተቃጠሉ ቆራጥ ሀገር አፍቃሪ በእርግጥ እርሳቸው ብቻ ነበሩ ተብሎ ተጽፏል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ በሪቻርድ ፓንክረስት ዕይታ በተሰኘው መጽሐፍ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ዕድገት ጥረት ያደረጉት የአጼ ቴዎድሮስ መነሳት ኢትዮጵያን ወደ አንድ አዲስ የታሪክ አቅጣጫ ለውጧታል ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ ተክለጻድቅ መኩሪያ አጼ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መጽሐፋቸው የቴዎድሮስ ጊዜ ከአንድ የታሪክ ዘመን ወደ ሌላ የታሪክ ዘመን ሽግግር የተደረገበት ድልድይ ነው ይላሉ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ የዘመናዊት ኢትዮጵያን መሠረት የጣሉ፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት የሠሩ ንጉሥ ናቸው ብለው ጽፈዋል፡፡ ከእርሳቸው በኋላም ለተነሱ ነገሥታት መንገድ የጠረጉ፣ መከራውን ተሸክመው፤ ጎዳናውን የቀየሱ ብልህና ጀግናም ናቸው፡፡
አጼ ቴዎድሮስ በዘመነ መንግሥታቸው በታላቅ የቤተ መንግሥት ሕንጻ ባማረ አዳራሽ ተቀምጠው፣ ዘውድ ደፍተው፣ በትረ መንግሥት ጨብጠው፣ በዙፋን ላይ ተንሰራፍተው፣ በወርቅ አልጋ እና በሚደላ ፍራሽ ላይ ተጋድመው፣ የዚህን ዓለም ንጉሣዊ አዱኛ ማጣጣም ሳያምራቸው ለራሳቸው ባርኔጣ፣ ከእግራቸው ጫማ ሳይፈልጉ፣ ያለ ምንም እረፍት እና መዝናናት ሳይፈልጉ፣ በድንኳን እየኖሩ፣ በከብት ጀርባ እና በእግራቸው ከአውራጃ ወደ አውራጃ በመዘዋወር፣ ዳገት ቁልቁለቱን፣ ሸለቆ እና ወንዛ ወንዙን በማቋረጥ ቆንጥር ለቆንጥር፣ በክረምት እና በበጋ በመንከራተት እየታገሉ ጉልበታቸውንም፣ አዕምሯቸውንም፣ በመጨረሻ ሕይወታቸውንም ሙሉ ለሙሉ ለሚወዷት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ሠውተዋል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት እና ውሕደት የሚወድ ይሁንም የወደፊቱም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህን ውለታ ተገንዝቦ የእኝህን ንጉሥ ስማቸውን በአክብሮት እና በአንድናቆት ሊዘክረው ይገባል ብለው ጽፈዋል ተክለጻድቅ መኩሩያ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ቴዎድሮስ በተሰኘው መጽሐፋቸው በመሳፍንት ተከፋፍላ የወደቀች ሀገራቸውን ለማንሳት የተነሱ ታላቅ ሀገር ወዳድ ነበሩ፡፡ ቴዎድሮስ በብዙ ገዥዎች ተቆራርጣ የነበረችውን ኢትዮጵያ እንደነበረችበት አንድ ለማድረግ ከፍተኛ ድካም ደክመዋል፡፡ ያለ እረፍት ሠርተዋል፡፡ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከተለያዩ መኳንንት አገዛዝ ባንድ መንግሥት ሥር እንድትተዳደር ለማድረግ የጥርጊያውን መንገድ የከፈቱ ዋናው መሐንዲስ ናቸው፡፡ ለአጼ ዮሐንስ እና ለአጼ ምኒልክ መጓዣውን መንገድ በሕይወታቸው የከፈቱ ቴዎድሮስ ናቸው ብለው መዝግበዋል፡፡
እኒህ ታላቅ ንጉሥ በደረስጌ ማርያም ቤተክርስቲያን ቅበዓ መንግሥቱን ተቀብተው፣ ዘውድ ደፍተው፣ በትረ መንግሥቱን ጨብጠው፣ ሰይፉን ታጥቀው፣ ጦሩን አስተካክለው፣ በአስፈሪው ዘውድ ላይ ተቀምጠው፣ በቀኝ እና በግራ እንደ አንበሳ በጀገኑ፣ እንደ ነበር በፈጠኑ ጀግኖች ታጅበው፣ በመኳንንቱ እና በሊቃውንቱ ተከበው፣ እልል እየተባለላቸው፣ ለክብራቸው እጅ እየተነሳላቸው፣ መለከት እየተነፋላቸው፣ ነጋሪት እየተጎሰመላቸው፣ ቅኔ እየተቀኘላቸው፣ ጎበዛዝቱ በፊታቸው ተንበርክከው እየፎከሩ እና እየሸለሉላቸው አጼ ቴዎድሮሰ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው የነገሡት በየካቲት አምስት ቀን ነበር፡፡
ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ስለ ንግሥናቸው ሲጽፉ የዚያኔው ደጅ አዝማች ካሳ ደጅ አዝማች ውቤን የካቲት ሦስት ድል አደረጉ፡፡ በሦስተኛው ቀን በየካቲት 5/1847 ዓ.ም ደጅ አዝማች ውቤ እነግስባታለሁ ብለው ባሠሯት እና ባስጌጧት በደረስጌ ማርያም እጨጌው በግራ ጳጳሱ በቀኝ ተቀምጠው መጸሐፈ ተክሊል እየተነበበ በአቡነ ሰላማ እጅ ሥርዓተ መንግሥት ተደርሶላቸው በመቀባት ቴዎድሮስ በተባለው ስመ መንግሥታቸው ነገሡ፡፡ ሲነግሡ የ35 ወይም የ36 ዓመት ጎልማሳ ናቸው፡፡ በዚሁ ቀን ባለቤታቸው ተዋበች አብረው ቆርበው ለእርሳቸው አክሊል ተደርጎላቸው እቴጌ ኾኑ፡፡
ከዚህ በኋላ ነጋሪት እየተጎሰመ ከዛሬ ጀምሮ ደጅ አዝማች ካሳ ስማቸው ቴወድሮስ ተብሎ ንጉሠ ነገሥት ኾነዋልና ደጅ አዝማች ካሳ ብለህ የጠራህ ትቀጣለህ ተብሎ ተነገረ ብለው ጽፈዋል፡፡ ለስመ መንግሥታቸው ቴዎድሮስ የሚለውን የመረጡበትን ምክንያት ሲናገሩም ቴዎድሮስ የሚባል ንጉሥ ተነስቶ ያለ ሰይፍ ያለ ጦርነት ይገባል፡፡ የተበላሸውን አሥተዳደር አስወግዶ ይነግሳል፡፡ በዘመኑ ሰላም እና ትክክለኛ ፍርድ ይኾናል፡፡ ግዛቱም እስከ ባሕር ነው እየተባለ ይነገር ነበር፡፡ እርሳቸውም ይህ ትንቢት የተነገረው ለእኔ ነው ብለው ያምኑ ስለነበር ነው ተብሎ ተመዝግቧል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ ስለ አጼ ቴዎድሮስ ንግሥና ሲጽፉ በየካቲት ወር በ1845 ዓ.ም አጼ ቴዎድሮስ ተብለው በደረስጌ ማርያም ቤተክርስቲያን በጳጳሱ አቡነ ሰላም እጅ ነገሡ ብለዋል፡፡ ቴዎድሮስ የነገሡበትን ዘመን ደብተራ ዘነበ እና አለቃ ወልደማርያም በጻፉት ታሪክ በ1847 ዓ.ም ነው ይላሉ፡፡ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ግን በ1845 ዓ.ም ነው ብለው ጽፈዋል፡፡ በእነዚህ መጻሕፍት የሁለት ዓመታት ልዩነት አለ፡፡ የእነ ደብተራ ዘነበ እና አለቃ ወልደማርያም የዘመን አገላለጽ ከኾነ ቴዎድሮስ የነገሡት አሥራ ሦስት ዓመታት መኾኑ ነው፡፡ አለቃ ታዬ አጼ ቴዎድሮስ አሥራ አምስት ዓመት ነገሡ ስለሚሉ የነገሡበት ዘመን ከአለቃ ተክለ ኢየሱስ ትረካ ጋር ይጣጣማል፡፡
መንግሥቱ ለማ የአባታቸውን የአለቃ ለማ ትረካ በጻፉበት መጽሐፈ ትዝታ ውስጥ አጼ ቴዎድሮስ በ1845 ዓ.ም ነግሠው በ1860 ዓ.ም ሞቱ ይላሉ፡፡ ባላንባራስ ማሕተመ ሥላሴም በዝክረ ነገር መጽሐፋቸው በ1845 ዓ.ም ነገሡ ይላሉ፡፡ ስለዚህ እኔም አብዛኛዎቹ በተናገሩት በ1845 ዓ.ም ነገሡ ብያለሁ ብለው ጽፈዋል ጳውሎስ ኞኞ፡፡
ገናናው ንጉሥ በዛሬ ቀን ነበር የነገሡት፡፡ በዛሬ ቀን ነበር ክብር እና ቅበዓ መንግሥቱን የተቀበሉት፡፡ የንግሥና ዘውዱንም የደፉት፡፡ እኒህ የአንድነት ምልክት፣ የጀግንነት ተምሳሌት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት መገለጫ የኾኑ ታላቁ ንጉሥ በታሰቡ ጊዜ የሀገር አንድነት ትታሰባለች፡፡ የሀገር ፍቅር ትታወሳለች፡፡ ጀግንነት እና ክብር ትነሳለች፡፡ እርሳቸው ልካቸው አንድነት፣ ጀግንነት እና አሸናፊነት ነው፡፡ እርሳቸው በበቀሉባት ምድር የበቀለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ እርሳቸው ሁሉ ሀገሩን ከወደዳት፣ ለክብሯ ከኖረላት ኢትዮጵያ ከፍ ከፍ ትላለች፡፡ እርሱም በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቅ ቀለም ይጻፋል፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት ያለዎትን ሁሉ ሰጥተዋልና ንጉሥ ኾይ ሁልጊዜም ይከበራሉ፡፡ ይዘከራሉ፡፡
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!