“አሁን የተገኘውን ሰላም በማጽናት በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በቁርጠኝነት ይሠራል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

52

ባሕር ዳር: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4 ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ሀሳቦች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በማብራሪያቸው ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል:-

👉 የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፖርክ የኤሌክትሪክ ችግርን ለመፍታት የሚሠራውን የቡሬ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ጨምሮ የክልሉን የመብራት ችግር የሚፈቱ ሌሎች ማከፋፈያ ጣቢያዎች እየተሠሩ ነው፡፡

👉 እንደ ክልል ከ600 በላይ ቀበሌዎች የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በጥናት ተለይተዋል፡፡

👉በፌዴራል መንግሥት በጀት የሚከናወኑ 61 እና በክልሉ በጀት ደግሞ 221 በአጠቃላይ 282 የመንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

👉 ተቋርጠው የቆዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደገና ወደ ሥራ እንዲገቡ ልዩ አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡

👉 ለመሠረተ ልማቶች ግንባታ ሲባል ከይዞታቸው ለሚነሱ ሰዎች ተገቢውን ካሳ ከፍሎ ወሰን የማስከበር ጉዳይ በቁርጠኝነት መፈጸም አለበት፡፡

👉 የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ለማሳደግ እየተሠራ ነው። የከርሰ ምድር ውኃ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች ሌላ የውኃ አማራጭ ተፈልጎ ተጠቃሚ እንዲኾኑም ይሠራል፡፡

👉 የጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ፋብሪካ ጠንካራ የአመራር ለውጥ አድርጓል፣ በቅርብ ጊዜ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ የሚገባበት አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡

👉 ደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ 37 በመቶ ደርሷል። በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ማስፋፊያ እና አዳዲስ ሥራዎችን የተመለከተ በጥናት ላይ የተመሠረተ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራም ነው፡፡

👉 በክልሉ የቴሌኮም አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን የበለጠ ለማሳደግ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

👉 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ 79 ቢሊዮን ብር ዋስትና አዘጋጅቷል። 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታሉ ቀድሞ ወደ ክልሉ ገብቷል። ከዚህ ውስጥም ከ1 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ደርሷል።

👉 የጸጥታ ችግሩን ተከትሎ የሚከሰቱ የግብይት አሻጥሮች እየተስተዋሉ ነው። በተለይም የነዳጅ ሕገ ወጥ ሥርጭት የኑሮ ውድነትን እያባባሰ በመኾኑ በትኩረት ተይዞ ይሠራበታል፡፡

👉 ማንኛውም አይነት የልማት ሥራ የሚከናወነው ጠንካራ የገቢ አሠባሠብ ሥርዓት ሲዘረጋ በመኾኑ የገቢ አሠባሠብ ሥራን አጠናክሮ ለመቀጠል ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡

👉 በክልሉ የትምህርት ሥርዓት ላይ ስብራት ገጥሟል። ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል። መምህራንም በታጠቁ ኀይሎች ወከባ እየደረሰባቸው ነው፤ የዚህን ድርጊት ቀጣይ ተጽዕኖ አርቆ በመመልከት የትምህርት ሥራን በጋራ ቆሞ መታደግ ግድ ይላል፡፡

👉የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ ተቋማት በሠሩት የተቀናጀ ሥራ የክልሉ እና የሕዝቡ ሰላም ተመልሷል፤ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በቁርጠኝነት ይሠራል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ አይነተኛ የሰላም ለውጥ ይመዘገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሁሉም ዘርፍ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እንደሚሠሩ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች ገለጹ፡፡
Next article“የአንድነት ምልክት፤ የጀግንነት ተምሳሌት”