ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ፈቃድ ሳያገኙ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ድሮን በሚያስነሱና በሚያበሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑ ተገለጸ፡፡

44

ባሕር ዳር: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የድሮን እና ሌሎች በራሪ አካላት አጠቃቀምን በተመለከተ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማንኝውም ዓይነት ድሮን ያለ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል በቅርቡ በመገናኛ ብዙኃን የተላለፈውን ማሳሰቢያ በማያከብሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡

በተለይ ከአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ቅንጅታዊ ስምሪቱን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማንኝውም አይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል መልዕክት የተላለፈ መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው፤ ብዙዎችም ይህን ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ማሳሰቢያውን በመጣስ ፈቃድ ሳያገኙ ድሮን ለማስነሳትና ለማብረር ሙከራ ያደረጉ አካላትን በጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ በመለየት ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ ተገቢው እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመልክቷል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ያመለከተው መግለጫው፤ በተለይ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ድሮኖች እና መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች የሚፈጥሯቸውን ስጋቶች ለመከላከል የሚያስችል በቂ የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ዝግጅት አድርጎ ወደ ስምሪት መግባቱን አስታውቋል፡፡

ከሥራ ጋር በተያያዘ ድሮኖችን መጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም አካል በ+251 983 00 02 98 እና +251 983 00 04 01 ስልክ ቁጥሮች በመደወል ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚችል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መግለጫ ያሳሰበ ሲሆን፤ ያለፍቃድ በሚኒሱ እና በሚበሩ ድሮኖች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለምክር ቤቱ ስለ በግብርናዎው ክፍለ ኢኮኖሚ ካነሷቸው አንኳር ጉዳዮች በጥቂቱ፡-
Next article“ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ አውታሮችን በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በመረጃ መደገፍ ይገባል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ