በደረሰው የእሳት አደጋ 18 ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።

72

ደብረ ብርሃን: የካቲት 05/2017 ዓ.ም(አሚኮ) በደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አየማን መናፈሻ እየተባለ በሚጠራው ቦታ በጋራዥ ላይ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ደርሷል። ቃጠሎው የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት አካባቢ ነው የደረሰው።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዋና ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ኪዳኔ በቀለ ለአሚኮ እንደተናገሩት በአደጋው 18 የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በርካታ የጋራዡ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። አደጋው እንደተሰማ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ወደ ስፍራው ቢያቀኑም ከፍተኛ ነፋስ ስለነበር ንብረቱን ማዳን ሳይቻል ቀርቷል ተብሏል። የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ከአደጋው ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ማዋል ተጀምሯልም ነው ያሉት። ምንም እንኳን በሕይዎት ላይ ጉዳት ባይደርስም በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ነው የተናገሩት።

በአደጋው የወደመውን ሀብት ጥቅል ግምት ለመሥራት መረጃ እየተሠበሠበ መኾኑን የተናገሩት ኮማንደር ኪዳኔ በየጊዜው የሚጠናቀሩ መረጃዎችን ፖሊስ ይፋ ያደርጋል ነው ያሉት።

በከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የእሳት አደጋ እየተበራከተ ነው ያሉት ኮማንደር ኪዳኔ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” የአምስት አዳዲስ እና ዘመናዊ ሆስፒታሎች ግንባታቸው በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ
Next articleበ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲመዘገብ እየሠራ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ገለጸ።