
ባሕር ዳር: የካቲት 05/2017 ዓ.ም(አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው። የምክር ቤት አባላት በየአካባቢው የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በጊዜ መጠናቀቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም የክልሉ መንግሥት ለመንገድ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ከምንግዜውም በላይ የላቀ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በክልሉ በጀት ብቻ 221 ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው፤ ከዚህ ውጥም 189 ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት የሚኾኑ ናቸው ብለዋል። ይህም የክልሉ መንግሥት ለመንገድ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ለመስጠቱ ማሳያ መኾኑን ነው ያነሱት።
በክልሉ መንግሥት በጀት ከሚሠሩት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በፌዴራል መንግሥት በጀት የሚሠሩ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ተናግረዋል። የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ እና ቀርበው በመደገፍ ፕሮጀክቶች በጊዜ እንዲጠናቀቁ እያመቻቹ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት ለበርካታ ዓመታት የሕዝብ የቅሬታ ምንጭ ኾነው የቆዩ ጅምር ፕሮጀክቶች ምላሽ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በፌዴራል መንግሥት ከተያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች አሁን ላይ ከ80 በመቶ በላይ ሥራቸው ተጠናቅቋል ነው ያሉት። በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ይበቃሉ ብለዋል። ሌላ ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በዝቅተኛ የአፈጻጸም ደረጃ ተገምግመው ወደተጠናከረ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑን አንስተዋል።
33 የሚኾኑ በፌዴራል ደረጃ የሚሠሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ መኾናቸው ተለይቶ የሚሠሩ ናቸው ብለዋል። 13 ፕሮጀክቶች ውላቸው መቋረጡን አንስተዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶችም እንደገና ውል ተይዞላቸው ወደተፋጠነ ሥራ እንዲገቡ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
ጥናት እና ዲዛይናቸው አልቆ የሚሠሩ እና ወደ ሥራ እየገቡ ያሉ ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ጠቁመዋል። የክልሉን የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ለማስፋት እንደመንግሥት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው በርካታ መሰናክሎች እየገጠሙ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የመሠረተ ልማት ግንባታ የሕዝብን ድጋፍ በእጅጉ ይሻል፤ ሰላምንም ይፈልጋል ነው ያሉት።
መንገዶች በሚሠሩበት ቦታ ላይ የሦስተኛ ወገን ባለቤትነትን የማስከበር ጉዳይ በፍጥነት ስለማይከናወን የመንገዶችን የግንባታ ሂደት እና የሥራውን ሰላም እንደሚያውክም ገልጸዋል። በመኾኑም በየአካባቢው የሚገኘው ማኅበረሰብ ለመንገድ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰላምን ማስጠበቅ እና ልማቱን ደግፎ ከዳር ማድረስ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!