“ኪራይ ነጻ ከማድረጋችን ባለፈ ነጋዴዎች በገበያ ላያ ዋጋ እንዳይጨምሩ የማግባባት ሥራ ተሠርቷል፡፡” የአዝዋ የንግድ አክሲዮን ማኅበር

176

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአዝዋ የንግድ አክሲዮን ማኅበር ለተከራዮች የአንድ ወር ኪራይ ሙሉ በሙሉ ነጻ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ የኮሮና ወረርሽኝን ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ተፅዕኖ በመረዳት እና ተከራዮች በገበያ መቀዛቀዝ መቸገራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚያዝያ ወር ኪራይን ሙሉ በሙሉ ነጻ አድርጓል፡፡

ኪራዩ ነጻ የተደረገው የቡቲክ፣ የስቴሽነሪ፣ የአልባሳት ስፌት እና ፎቶ ቤቶች እንዲሁም በሌሎቸ የንግድ ሥራዎች ለተሰማሩ 48 ነጋዴዎች ነው፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሊቀ መንበር እንዳልካቸው ላቀው እንደተናገሩት ነጻ የተደረገው ኪራይ ወደ ገንዘብ ሲቀየር 297 ሺህ 860 ብር ነው፡፡ ኪራይ ነጻ ከማድረግ በተጨማሪም ተከራዮች አንዴ ይከፍሉት የነበረውን የስድስት ወር ቅድሚያ ክፍያ ወደ ሦስት ወር ዝቅ እንዲል ተወስኖላቸዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ቀደም ብሎ በከተማዋ ድጋፍ የሚፈልጉ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት አቶ እንዳልካቸው ለወረርሽኙ መፍትሔ እስከሚገኝም የተለያዩ ማስተካከያዎችን በማድረግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የአዝዋ የንግድ አክሲዮን ማኅበር ሕንጻ ገንብቶ የንግድ ሱቆችን ማከራየት ከጀመረ አራት ዓመታት ሆኖታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኪራይ ጭማሪም አለማድረጉን ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡

“ኪራይ ነጻ ከማድረጋችን በተጨማሪ ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ አስገንዝበናል” ብለዋል፡፡ ወረርሽኙ ወደ ሀገር ከገባ ጊዜ ጀምሮ በገበያ ማዕከሉ የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል አሠራር እንዲኖር እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ተከራዮችም የአዝዋ የንግድ አክሲዮን ማኅበር ላደረገላቸው የኪራይ ቅናሽ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ የስድስት ወሩን ቅድመ ክፍያ ወደ ሦስት ወር መቀነሱ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል፡፡ በልብስ ስፌት እና ዲዛይን ሥራ የተሠማሩት አቶ ከድር እስማኤል እንዳሉት ወረርሽኙን ተከትሎ የገበያ መቀዛቀዝ መፈጠሩ ነጋዴዎችን እየጎዳ በመሆኑ መደጋገፍና መተባበር ተገቢ ነው፡፡

ምንም እንኳን የአቅርቦት ችግር ቢኖርም ወቅቱ መረዳዳት የሚያስፈልገው በመሆኑ ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ የተዘጋጁ ልብሶችን በመሸጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው አበባ ታደሰም ይኸንኑ ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡ አልባሳቱ ወረርሽኝ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ የገቡ ስለሆነ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያደርሳቸው ነገር እንደሌለ በመግለጽም የዋጋ ጭማሪ አለማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ፈታኙን ወቅት ለመሻገር የንግዱ ማኅበረሰብ ዋጋ ባለመጨመር የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የተናገሩት ነጋዴዎቹ አቅማቸው በፈቀደ መልኩ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ደንበኞች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleከ43 ሺህ በላይ ሰዎች የሰውነት ሙቀት ልኬታ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡
Next articleየሚሰበሰበው ደም መልሶ ለቤተሰብ የሚያገለግል በመሆኑ ማኅብረሰቡ ደም እንዲለግስ ጥሪ ቀረበ፡፡