
እንጅባራ: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደደር ከ 850 ሚሊዮን ብር በላይ በሚኾን ወጭ 19 ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጄክቶች እየተገነቡ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ አስታውቋል። መምሪያው የ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት የሥራ አፈፃጸሙን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ መስኖ እና ቆላማ አከባቢዎች ልማት መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ቢተው ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የበርካታ የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር የውኃ ፀጋዎች ባለቤት መኾኑን ገልጸዋል። ነገር ግን በመስኖ መልማት ከሚገባው መሬት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ እየለማ ያለው 30 በመቶ ብቻ መኾኑን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በመስኖ የማልማት አቅምን የሚያሳድጉ 19 ፕሮጀክቶች ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ በሚኾን ወጭ በመገንባት ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ3 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ያሉት ኀላፊው ከ4 ሺህ 300 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንደኾኑም አንስተዋል።
እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች በጥራት እና በተቀመጠላቸው ጊዜ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ መምሪያው ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ፕሮጀክቶቹ መስኖን በማዘመን ለምርት እና ምርታማነት ዕድገት ያላቸው ፋይዳ የጎላ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ለሥራው ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!