የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽን ሥራ ጀመረ፡፡

107

አዲስ አበባ: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ130 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን በመገንባት ረገድ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽኑን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት ኢትዮቴሌኮም ዘመኑ የደረሰበትን አልትራ ፋስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽን አስጀምሯል፡፡

በሀገሪቱ የመጀመሪያ የኾነውን የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዮች ጉባኤ ሊካሄድ ቀናት በቀሩበት ዋዜማ ሥራ ማስጀመር መቻሉ የሀገርን ገጽታ ከፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት፡፡ ዛሬ በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽን “አልትራ ፋስት ኢቪ ቻርጂንግ” የሚል ስያሜ ያለው ነው፡፡

ስቴሽኑ እጅግ ዘመናዊ እና ምቹ በመኾኑ አንድ ኪሎ ሜትር የሚያስጉዝን ርቀት በአንድ ሰከንድ ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ ቻርጀር መኾኑን ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከቦሌ ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ ላይ ተገንብቶ ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው አልትራ ፋስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽን ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ የተገጠመለት እጅግ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽን ነው፡፡

ይህም በኢትዮጵያም የመጀመሪያው ስቴሽን ሲኾን ሌላ ሁለተኛ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽንም በመዲናዋ ሌላኛው አካባቢ እየተገነባ እንዳለ እና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ ተናግረዋል፡፡ ከቦሌ ወደ መገናኛ ባለው መንገድ መሐል ላይ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው “አልትራ ፋስት ኢቪ ቻርጅንግ” በ1 ሰከንድ 1ኪሎ ሜትር ወይም በ5 ደቂቃ 200 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚያስችል ቻርጀር ስለመኾኑም ተገልጿል፡፡

ይህ አልትራ ፋስት ቻርጀር አሁን ባለው የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንደየ ተሽከርካሪዎቹ ዓይነት ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል ሲኾን ተጠቃሚዎች ይህንን ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ሲጠቀሙ ያለማንም አጋዥ ክፍያውን በቴሌ ብር በመክፈል ቻርጅ ማድረግ እና መጠቀም እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ እንደዚህ ዔይነት ዘመናዊ አሠራሮችን ኢትዮ ቴሌኮም ጀምሯል ሌሎች የግል ባለሃብቶች ደግሞ ይህን አሠራር ተከትለው መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ለከተሞች ዕድገት፣ ለንፁህ ትራንስፖርት እና ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መኾን ሁሉም በጋራ እንዲሠራም መልዕክት አስተላልፈዋል::

ዘጋቢ፡- ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል” ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ
Next article19 ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጄክቶች እየተገነቡ መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።