“የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል” ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ

37

ባሕር ዳር: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማነት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጥሪ አቅርበዋል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር በምክክሩ ሂደት እና ተሳትፎ ዙሪያ ዛሬ ውይይት አድርጓል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለሠራው ሥራ እና ላስመዘገበው ውጤት የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ስኬታማ ውጤቶችን እንዲያስመዘግብ የሃይማኖት ተቋማት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ የሚደረገው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተሳካ እንዲኾን የሃይማኖት ተቋማት የተለመደውን ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ.ር) በበኩላቸው ኮሚሽኑ በሦስት ዓመታት ጉዞ ያከናወናቸውን ሥራዎች እና ቀሪ ተግባራትን አስመልክቶ ለሃይማኖት አባቶች ገለጻ አድርገዋል።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሃይማኖት ተቋማት የሚሳተፉበት የአሰራር ሥርዓት ምክረ ሃሳብ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ኮሚሽኑ በብዙ ፈተና እና ውጣ ውረድ ውስጥ ኾኖ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እየተወጣ ያለውን ታሪካዊ ኀላፊነት አድንቀዋል። ከቀረበው የአሰራር ስርዓት ምክረ ሃሳብ በመነሳት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሃይማኖት ተቋማት ሊሳተፉ የሚችሉበትን ሁኔታ በምክር ቤታቸው በኩል ወስነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኮሚሽኑ እንደሚያሳውቁም ጠቁመዋል።

ከውይይቱ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት እንዲኾኑ ያዘጋጀቻቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማስረከቧን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በትኩረት እየተሠራ ነው” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት
Next articleየመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽን ሥራ ጀመረ፡፡