
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ከጥር 23/2017 ዓ.ም እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የጠንካራ ፓርቲ ግንባታን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ዘላቂ ሰላም መፍጠር፣ የኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠን እና ሌሎችንም የውሳኔ አቅጣጫዎች ማስቀመጡ ይታወሳል።
ፓርቲው በመደበኛ ጉባኤው ላይ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት ላይ የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የጎዛምን ወረዳ መሪዎች ውይይት አካሂደዋል። በውይይት መድረኩ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የኔነህ ሁነኛው በጉባኤው የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መሪዎች የሚተጉበት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ መሪዎች ፓርቲው በመደበኛ ጉባኤው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ተግባራዊ በማድረግ ለኅብረተሰቡ ሰላም መጠበቅ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፓለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ገነት በቀለ ፓርቲው በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ለዘላቂ ሰላም መምጣት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፉ ቀጣይነት ያላቸውን መድረኮች በማካሄድ ፓርቲው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ተፈፃሚ እንዲኾኑ ይሠራልም ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊ መሪዎች በጎዛምን ወረዳ አሥተዳደር በመንግሥት ተቋማት እየለሙ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!