“ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች” አቶ አሕመድ ሽዴ

28

ባሕር ዳር: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ለ20 ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገለጹ። 23ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ጉባዔ የካቲት 112017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ሚኒሰትሩ የኢኒሼቲቩን የአምስት ዓመታት አፈፃፀም እና የቀጣይ ዕቅድ አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እስካሁን ከሃብት አሠባሠቡ ጋር በተገናኘ ለቀጣናው ሀገራት በኢኒሼቲቩ ለቀጣናው ሀገራት 15 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት በመነሻነት ለማሠባሠብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ከዚህም ውስጥ ወደ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላሩ ለፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ውሏል። ኢትዮጵያም 20 ለሚኾኑ ፕሮጀክቶች ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች ብለዋል። ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በነበረው የድርቅ አደጋ የድርቅ መረጃ ጠቋሚ መድኅን መሠረት ያደረገ ሰፊ ሽፋን በቆላማ አካባቢዎች ተግባራዊ ተደርጓል። በርካታ የውኃ መሠረተልማት ግንባታዎች በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች ተገንብተዋል፡፡

ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ 500 ሺህ ሄክታር መሬት ከአንበጣ ወረራ ለማዳን ተችሏል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር አሳድጓል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ኢኒሺዬቲቩ ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የመጣውን ሪፎርም እና በቀጣናው ሀገራት የተጠናከረ ግንኙነት ተከትሎ የተመሠረተ ነው፡፡ ዓላማውም በቀጣናው ያሉ ሀገራትን በኢኮኖሚ ትብብር የሚያስተሣሥሩ የልማት ፕሮጀክቶችን መተግበር ነው።

የኢኒሺዬቲቩን መመሥረት ተከትሎ የልማት አጋሮች በቀጣናው ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያን፤ ጅቡቲን ኤርትራን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን፤ ሱዳንን እና ደቡብ ሱዳንን ያቀፈ ነው። በቀጣናው የመሠረተ ልማት ትስስር ማጎልበት፣ የንግድ እና ኢኮኖሚ ውህደትን ማጠናከር፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮችን የመቋቋም አቅምን መገንባት እና የሰው ኀይል ልማትን የሚያጠነክሩ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶች ይደገፉበታል።

የዓለም ባንክ፤ የአውሮፓ ኅብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ እንዲሁም በተባባሪነት የሚሠሩ እና የኢጋድ ሴክሬታሪያት ከጥንስሱ ጀምሮ ሲደግፉ የነበሩ ናቸው። ኢኒሺዬቲቩ የጀርመን እና የእንግሊዝ መንግሥትን ተጨማሪ አጋር ሀገራት በማድረግ ተቀብሏል።

እንደ ኢፕድ ዘገባ የ23ኛው የፋይናንስ ሚኒስትሮች ሥብሠባ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓም በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል። በጉባኤው የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የጀርመን እና የእንግሊዝ መንግሥት ተወካዮች፣ የአረብ ባንክ፣ የአሜሪካ እና የኔዘርላንድስ መንግሥት ተወካዮች በታዛቢነት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኮሪደር ልማቱ ማኅበረሰቡ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል” አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ
Next article“ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በትኩረት እየተሠራ ነው” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት