“በኮሪደር ልማቱ ማኅበረሰቡ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል” አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ

30

ደሴ: የካቲት 04/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት በከተማዋ የተከናወኑ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሰላም ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በሰጡት መግለጫ በቅርቡ የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችን መሠረት በማድረግ በከተማዋ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትንም ጠቁመዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው ብልጽግና ፓርቲ የከተማዋን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት እና የመልካም አሥተዳር ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። የሕዝብ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ መመለስ እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በርካታ ነጋዴዎችን፣ ምሁራንን፣ ወጣቶችን፣ አንቀሳቃሾችን እና ሌሎችንም በማሰባሰብ ሕዝብን ያሳተፉ በርካታ ልማቶችን ማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል። በጤናው ዘርፍ በተደረገው የማስፋፊያ ግንባታ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ብር የሚደርስ ተግባር መከናወኑንም አንስተዋል። በትምህርቱ ዘርፍ ደግሞ በ16 ትምህርት ቤቶች የአዳዲስ ክፍሎች ግንባታ እና ጥገና በማድረግ በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ በጥቅሉ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደረጎ ተግባራት ተከናውነዋል።

የተማሪዎች ምገባም ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግሥት እና በአጋዥ አካላት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ አበረታች ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል ። የከተማው ማኀበረሰብ ጥያቄ የነበሩ 11 የአሰፖልት ንጣፍ መንገድ ሥራዎች ተጀምረው ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል ቀሪዎቹም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።

ሁለት መናኽሪያ መገንባታቸውን ተናግረዋል። ይህ የሚያመላክተው ፕሮጀክትን ጀምሮ መጨረስ የብልጽግና ፓርቲ ዋናው እሳቤ መኾኑን ነው ብለዋል። በከተማዋ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው የመብራት የኃይል እጥረት አንዱ ነበር ያሉት አቶ ሳሙኤል ችግሩን ለመፍታት በፌዴራል መንግሥቱ አማካኝነት በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጭ የማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።

የከተማዋን የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ችግር ለመፍታት በፌደራል መንግሥት 650 ሚሊዮን ብር ተመድቦ በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና በሌሎችም አካባቢዎች ኘሮጀክቶች በመሠራት ላይ መኾናቸውን አስረድተዋል። “በከተማዋ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ማኅበረሰቡ እስከ አሁን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን” ተናግረዋል። ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ሁሉን አካታች መሠረተ ልማት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

ብልጽግና ፖርቲ ሰው ተኮር ፓርቲ ነውም ብለዋል። በፓርቲው መሪነት ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ተናግረዋል። የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመፍታት በኩልም 2 ሺህ 980 ዜጎች ከ10 ዓመት በላይ የቆየ ችግራቸው እንደተፈታላቸው ገልጸዋል። በሕገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ ከ47 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማስመለስ ለከተማዋ እድገት እንዲውል ተደርጓልም ነው ያሉት።

መንግሥት እና ማኅበረሰቡ በመደማመጥ እና ሰፋፊ የግንዛቤ መድረኮችን በመፍጠር በተሠራው ሥራ ከተማዋ ሰላማዊነቷን አስጠብቃ ቀጥላለች ነው ያሉት። በቀጣይ ከተማዋን የማዘመን ሥራዎች በተለይም የመልሶ ማልማት ሥራ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ተደራሽነት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር፣ የተረጋጋ ሰላም ማስፈን እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ለማኅበረሰቡ ሚዛናዊ እና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት በሚዲያ እና በሕዝብ ግንኙነት ዘርፉ ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የተደገፈ ሥራ ይሠራል ብለዋል።

በብልጽግና ፖርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱን የተመለከትንበት ነውም ብለዋል። የተሰጡ አቅጫዎችን በጊዜ የለኝም መንፈስ ማኅበረሰቡን በማቀናጀት ይሠራል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ3 ሚሊዮን 112 ሺህ በላይ ሰዎች የወባ በሽታ ምርመራ አገልግሎት አግኝተዋል” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next article“ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች” አቶ አሕመድ ሽዴ