ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ተግባር ላይ ኅብረተሰቡ አጋዥ እንዲኾን ተጠየቀ።

24

ጎንደር: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ዙሪያ ከዞን እና ከወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ ባለፉት ወራት የነበሩ ግጭቶችን ወደ ዘላቂ ሰላም ለመመለስ የተደረገው ጥረት፣ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የተጀመረው የበጋ መስኖ ልማት ሥራዎች በጥንካሬ ተነስተዋል።

በአንጻሩ የኑሮ ውድነቱን በታቀደው ልክ መቀልበስ አለመቻሉ፣ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈለገው ልክ አለመኾኑ፣ የጤና መድኅን አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አለመዘመን እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው በድክመት ተነስቷል።

በውይይቱ የተሳተፉት የምስራቅ ደንቢያ አሥተዳዳሪ ሀብቴ ብርሌ ባለፉት ወራት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ እና በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል። በተካሄዱ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶች የነበረውን ሰላም በአንጻሩ መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።

የተግባር እና የአመለካከት አንድነት እንዲመጣ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሰርካለም ሊጋባው በኅብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነቱን ለማስታገስ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን የነገሩን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁ ናቸው። ታጥቀው እየተንቀሳቀሱ የነበሩ ወንድሞች በሰላማዊ መንገድ ኅብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል። በዚህም ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እና የዕለት ከዕለት ሥራውን እንዲከውን አግዟል ነው ያሉት።

በተጀመረው ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ተግባር ላይ ኅብረተሰቡ አጋዥ እንዲኾንም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“1 ሺህ 40 የሚኾኑ ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ ይጠናቀቃሉ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“ከ10 ሚሊዮን በላይ የአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍት ታትሟል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ