
የቤት ለቤት የኮሮና ቫይረስ የሰውነት ሙቀት ምርመራ መጀመሩን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና ጥበቃ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች የሰውነት ሙቀት ልኬታ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ደስታው ክብረት እንደተናገሩት በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል በሰባቱ የቤት ለቤት የሙቀት ልኬታ መመርመር ተጀምሯል፡፡ ጎንደር ዙሪያ፣ ታች አርማጭሆ፣ አለፋ፣ ላይ አርማጭሆ፣ ጠገዴ፣ ጣቁሳና ጭልጋ ወረዳዎች ናቸው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙት፡፡ በተጠቀሱት ወረዳዎች 13 ሺህ 620 ቤቶች ተጎብኝተዋል፡፡ እስካሁን 43 ሺህ 401 ግለሰቦች የሰውነት ሙቀት ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡ በተደረገው ምርመራ ከኮሮና ቫይረስ በሽታ ጋር ተቀራራቢ ምልክት ያሳዩ ግለሰቦች ተለይተው ናሙና ወደ ባሕር ዳር ተልኮ ከበሽታው ነፃ መሆናቸው በምርመራ መረጋገጡንም አስታውቀዋል፡፡
በቀሪዎቹ የዞኑ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮችም ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ መምሪያው አስታውቋል፡፡ የቤት ለቤት አሰሳ የሚያደርጉ 500 የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና ወስደው ወደ ተግባር መግባታቸውንም ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ ወረርሽኑን ከወዲሁ ለመከላከል ያመች ዘንድም ወደ ዞኑ በሚያስገቡ ዋና ዋና መንገዶች ተመሳሳይ ሥራዎች እየተከናወኑም ነው ተብሏል፡፡
ከትግራይ ክልል በዳንሻ በኩል የሚገቡ መንገደኞች ሶሮቃ ከተማ፣ ከምዕራብ ጎንደር በመተማ በኩል የሚመጡትን ጭልጋ (ሰራባ)፣ በቋራ ወረዳ በኩል የሚገቡት ሻውራ ከተማ እንዲሁም በባሕር ዳር አቅጣጫ የሚያመሩት ደግሞ እንፍራንዝ ከተማ ላይ የሰውነት ሙቀት ልኬታ እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ