
ባሕር ዳር: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። በጉባኤው የተገኙት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን መንግሥት የስድስት ወራት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው።
ርእሰ መሥተዳድሩ የ2017 ግማሽ በጀት ዓመት የክልሉን የወጭ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ከጸደቀው 150 ነጥብ 6 ቢሊዮን በጀት ውስጥ ባሳለፍናቸው ስድስት ወራት 34 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል። ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ሥራዎች ማስፈጸሚያ 30 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል።
ቀሪው 3 ነጥብ 59 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለካፒታል ሥራዎች የወጣ ስለመኾኑ ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል። ያለውን ውስን ሃብት በመጠቀም የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በዚህ ዓመት ለመመረቅ እና ወደ ልማት ለማስገባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል 17 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር መመደቡንም ተናግረዋል። 1 ሺህ 40 የሚኾኑት ፕሮጀክቶች በ2017 በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቁም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!