
ፍኖተ ሰላም፡ የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በፓርቲው ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የሚመክር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው። በብልጽግና ፓርቲ የተቀመጡ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን ለሥራ ኀላፊዎች ግንዛቤ በመፍጠር ተፈጻሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ የብልጽግና ፓርቲ የምክር ቤት አባል እና የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ገልጸዋል።
ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት። በጸጥታው ችግር ምክንያት የሚስተዋሉ የፍትሕ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን ለመቅረፍ ከመሪዎች ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግም ዋና አሥተዳዳሪው ጠቁመዋል።
እንደ ሀገር የተቀመጡ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን ተፈፃሚ ለማድረግ የመሪዎችን አቅም በየጊዜው በማሻሻል ማኅበረሰቡን በትጋት ማገልገል እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ ናቸው።
በማኅበረሰቡ ዘንድ ለበርካታ ዓመታት ሲነሱ የነበሩ እና በጸጥታው ችግር ምክንያት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ተይዟል ብለዋል። ማኅበረሰቡን ለምሬት የዳረጉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እና ከጸጥታው ችግር ጋር በተያያዘ የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አጉማስ አንተነህ ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!