
ባሕር ዳር: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባዔ የመጀመሪያ ቀን ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ነው። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን መንግሥት የስድስት ወራት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው።
ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ መንግሥት ሲተገበሩ የቆዩ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሞችን ቀዳሚ አድርገው አቅርበዋል። የክልሉን አጠቃላይ ምርታማነት ማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን መቀነስ፣ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እና የገቢ እና የውጭ ንግድ ሚዛንን ማስጠበቅ ታቅደው በትኩረት የተከናወኑ ሥራዎች ናቸው ብለዋል።
የ2016 በጀት ዓመት የክልሉ ጠቅላላ የምርት መጠን በገንዘብ ሲተመን 370 ነጥብ 64 ቢሊዮን ነበር ነው ያሉት። የክልሉ ጥቅል ምርት ዕድገት 6 በመቶ ኾኖ መመዝገቡንም አንስተዋል። የ2017 በጀት ዓመት የክልሉ ጠቅላላ የምርት መጠን በብር 395 ነጥብ 85 ቢሊዮን እንደሚኾን በትንበያ ስለመጠቆሙም ተናግረዋል። ይህም ጥቅል የምርት ዕድገቱን ወደ 6 ነጥብ 8 ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ለልማት እንቅፋት ኾኖ የቆየው የክልሉ የሰላም እጦት እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከዚህ በላይ ከተጋን ከትንበያው በላይ የምርት ዕድገት ስኬት እናስመዘግባለን ብለዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ እንደ ምርት መደበቅ፣ ምክንያታዊ ያልኾነ የዋጋ ጭማሪ፣ የምርት እንቅስቃሴን መግታት እና የመሳሰሉ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ ድርጊቶች እንደሚከሰቱ ጠቅሰዋል። ሁሉም በጋራ ተረባርቦ ሊያስወግዳቸው ይገባል ነው ያሉት።
በክልሉ ተከስቶ የቆየውን የጸጥታ ችግር በመፍታት በከፍተኛ የኑሮ ጫና ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ኅልውና ማረጋገጥ ለነገ የማይተው ተግባር ነው ብለዋል። በቀጣይ የበጀት ዓመቱ የሥራ ጊዜያት በትኩረት ተይዞ የሚሠራበት ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል። ከመንግሥት ተዘዋዋሪ በጀት ጭምር 1 ቢሊዮን ብር በመመደብ የኑሮ ውድነትን የማርገብ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት የሥራ ጊዜ ውስጥ ለ493 ሺህ 497 ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 286 ሺህ 139 ያህሉ ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል። ከተፈጠረው የሥራ እድል ውስጥም 34 ሺህ 394 የሚኾኑት የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ዕድል ያገኙ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የሥራ አጥነት ችግር በክልሉ አሳሳቢ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፤ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት መፈታት አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!