ምክር ቤቶች የጋራ ትርክቶችን በመገንባት ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ አሳሰቡ።

28

አዲስ አበባ: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል አፈ ጉባኤዎች በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት “ምክር ቤታችን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታችን” በሚል መሪ መልዕክት እየመከሩ ነው። የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ኬረዲን ተዘራ (ዶ.ር) ምክር ቤቶች የጋራ ትርክት፣ የሰላም እሴት እንዲሁም የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ላይ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል።

እንደ ሀገር ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሠሩት ሥራዎች የተሻለ ለውጥ መምጣት መቻሉንም ሚኒስትር ድኤታው ገልጸዋል። በተለይም በሀገራዊ ማንነት እና በሀገራዊ ጥቅም ላይ ዜጎች የተቀራረበ እሴት እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ምክር ቤቶች ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ መኾኑንም ዶክተር ኬረዲን ተናግረዋል።

በቀጣይም ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ምክር ቤቶች ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል በመውረድ የጋራ ትርክት ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ሎሚ በዶ ኢትዮጵያ ብዝኀ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ዕምነት እና ብሔር ያላት ሀገር እንደመኾኗ መጠን እንደ ትላንት አባቶቻችን ሀገራዊ ማንነቶችን እና ልዩነቶችን በፍታሃዊነት በማስተናገድ ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ኀላፊነት አለብን ብለዋል።

ሀገረ መንግሥትን፣ ኅብረብሔራዊ አንድነትን እና የጋራ ትርክትን በመገንባት ረገድ አሁንም ቢኾን ብዙ የሚቀሩ ያልተሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ምክትል አፈ ጉባኤዋ አንስተዋል። ሰላሟ የጸና እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር ለአዲሱ ትውልድ ለማሰረከብ ምክር ቤቶች በኅብረተሰቡ ዘንድ አሠባሣቢ የኾኑ የጋራ ትርክቶችን መገንባት ይገባቸዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የተሟላ ግንዛቤ በመያዝ ለሕዝብ ተጠቃሚነት መሥራት ይገባል” የደብረታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን
Next article“የ2017 በጀት ዓመት የክልሉ ጠቅላላ የምርት መጠን 395 ነጥብ 85 ቢሊዮን እንደሚኾን ይጠበቃል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ