
ባሕር ዳር: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም የመንግሥታት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው።
ልዑክ ቡድኑ ዱባይ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዑመር ሁሴን (ዶ.ር) እና ዲፕሎማቶች አቀባበል ተደርጎለታል።
በጉባዔው የኢትዮጵያ ልዑክ በከፍተኛ ደረጃ የሁለትዮሽ፣ ባለ ብዙ ወገን መድረኮች፣ በፓናል ውይይቶች በጎንዮሽ መስተጋብራዊ ክፍለ ጊዜዎች ላይ ተሳትፎ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባዔው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ውጤታማ ፖሊሲ ማውጣት፣ የዜጎች ተሳትፎ፣ ዘላቂ ልማት፣ የውኃና መስኖ አጠቃቀም እና የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎች የመድረኩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚኾኑ ተመላክቷል።
ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ መንግሥታዊ የአሥተዳደር አቅምን በሚያዳብሩ ዓለም አቀፋዊ ስጋቶች እና እድሎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!