
ደብረ ብርሃን: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከፍታ ለደብረብርሃን” በሚል መሪ መልዕክት ሀገር አቀፍ የንግድ ትርዒት እና ባዛር በደብረብርሃን ከተማ ተጀምሯል። የደብረ ብርሃ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ይርጋለም ምሥጋናው ባዛሩ ሸማቹን እና አምራቹን በአንድ ቦታ በማገናኘት በኩል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ሸማቹ ማኅበረሰብ የሚፈልጋቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ዕድል ይሰጣልም ብለዋል፡፡ በንግድ ትርዒት እና ባዛሩ ላይ የተለያዩ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች እና ሸቀጦችም ቀርበዋል፡፡ ከቀረቡት የግብርና ምርቶች መካከል ቀይ ጤፍ በኩንታል ከ9 ሺህ 500 እስከ 10 ሺህ፣ ነጭ ጤፍ በኩንታል ከ11ሺህ 900 እስከ 12 ሺህ 500 ብር እንዲሁም ማሽላ በኩንታል ከ5 ሺህ እስከ 6ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
የቢሮና ቤት መገልገያ እቃዎች በዚህ ባዛር ላይ በስፋት ተገኝተዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በርካታ ተሳታፊ ያላቸው የአንድ ቦታ የግብይት አማራጮች መጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡ አምራቾችን እና ሸማቾችን በማገናኘት አመቺ የግብይት ሰንሰለት መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ዓላማ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አማረ ተክለዮሐንስ በባዛሩ ላይ 150 የሚደርሱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ነጋዴዎች የሚሳተፉ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የንግድ ትርዒት እና ባዛሩ እስከ የካቲት 14/2017 ዓ.ም ድረስ ክፍት ኾኖ ይቆያልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ወንዲፍራ ዘውዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!