“ሰላም ከሁሉም ይቀድማል” የደባርቅ ከተማ ሴቶች

40

ደባርቅ: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የሴቶች የተደራጀና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ዞናዊ የሴቶች ንቅናቄ መድረክ በደባርቅ ከተማ ተካሂዷል። የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሴቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ ይጠቀሳል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመኾኑ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ከንግግር ባለፈ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። ወይዘሮ ፈንታ ተክሉ የተባሉ በደባርቅ ከተማ የደብር ቀበሌ ነዋሪ እንደገለጹት ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ መብላት ከባድ ብቻ ሳይኾን የማይታሰብ ነው ብለዋል።

የዞኑ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዝማም አቡሃይ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከምንጊዜውም በላይ የሴቶች፣ ሕጻናት እና አካል ጉዳተኞች ተጋላጭነት መጨመሩን ተናግረዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ባንችአምላክ መልካሙ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ሂደት የሚጀምረው ከቤተሰብ በመኾኑ ሴቶች በየቤታቸው የሰላም አምባሳደር መኾን መቻል አለባቸው ብለዋል። ጥቃቶችን ለመከላከልና ሲከሰቱም አፋጣኝ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ለማስቻል ሰላም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አስራት ይበይን ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዘርፎች የሴቶች ተጠቃሚነት መዳከሙን ገልጸዋል። በቀጣይም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ለማሳደግ በቅድሚያ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ሊግ ኀላፊ እና የዞኑ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አማካሪ ሳምራዊት አዛናው በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የልማት ሥራዎች የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበቀጣይ ሦስት ዓመታት ለ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ገለጸ።
Next articleሀገር አቀፍ የንግድ ትርዒት እና ባዛር በደብረ ብርሃን ከተማ ተከፈተ።