
ባሕር ዳር: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግጭት እና ሌሎች ችግሮች ዜጎችን ለአዕምሮ ጤና ቀውስ እና ለሥነ ልቦና ጫና ይዳርጋቸዋል። በግጭት ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች ሀብታቸውን፣ ንብረታቸውን እና ጤናቸውን ያጣሉ። ይህ ደግሞ ማኅበራዊ ችግርን ይፈጥራል። በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ወገኖች ለሥነ አዕምሮ ጤና ችግር እና ለሥነ ልቦና ጫና መጋለጣቸው ተመላክቷል።
በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፎረም ጸሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ዘርፈ ብዙ ቀውስ አምጥቷል ብለዋል። የሥነ አዕምሮ ጤና እና የሥነ ልቦና ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል። በግጭት ወቅት ሴቶች እና ሕጻናት ተጎጅዎች ናቸው ብለዋል።
ምሁራን በቅንጅት በመሥራት ማኅበረሰባቸውን መታደግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። በዘመናት ሂደት ውስጥ ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ ያሉት ጸሐፊው ማኅበረሰቡ በርካታ ችግሮች አጋጥመውታል፣ ነገር ግን ይህ ችግር እና አስቸጋሪ ወቅት አንድ ጊዜ እንደሚያልፍ ማመን አለበት ነው ያሉት።
ከአባቶቻችን የተማርነው ችግሮችን በጽናት ማለፍ ነው ብለዋል። ይሄን ወቅት ለማለፍም በኅብረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። በጣም ጠንካራ መኾን እንደሚገባም ገልጸዋል። ከግጭት እና ከሌሎች ችግሮች ጋር ተያይዞ በማኅበረሰቡ እየደረሰ ላለው የሥነ አዕምሮ ጤና እና የሥነ ልቦና ችግር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።
መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማትን አስተባብረን ኅብረተሰቡን መታደግ አለብንም ብለዋል። በየቀኑ የሚሰማው እና የሚታየው ልብ ሰባሪ ጉዳይ ለአዕምሮ ጤና እና ለሥነ ልቦና ችግር ተጋላጭ ያደርጋል ነው ያሉት። አባቶቻችን በጣም ጠንካሮች ስለነበሩ ብዙ የመከራ ጊዜያትን አሳልፈዋል ያሉት ጸሐፊው እኛም ይሄን ጊዜ እንደምናልፈው ማመን ይገባናል ብለዋል። ችግሩን ለማለፍ በሙያ የተደገፈ እገዛ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም ኾነው ማኅበረሰብን እንደሚደግፉም አንስተዋል።
የምርምር ሥራዎቻቸው እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራቸው የክልሉ ሕዝብ ካለበት አሁናዊ ችግር አንጻር እንዲቃኝ ተሠርቷል ነው ያሉት። የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አመላክተዋል። የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎታቸው እና የምርምር ሥራዎቻቸው በችግር ውስጥ ያለውን ሕዝብ የሚያወጣ መኾን አለበትም ብለዋል። በግጭቱ ምክንያት በርካታ ወገኖች በድባቴ ውስጥ መኾናቸውንም አንስተዋል። የምሁራን ዝምታ መፍትሔ አይደለም ያሉት ጸሐፊው ከችግሩ ለመውጣት የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ምሁራን ማኅበረሰባቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ችግሩ በዘላቂነት እንዲቀረፍ ምሁራን ሙያዊ አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። የትኛውንም የፖለቲካ ወግንና ሳይዙ ሕዝብን መሠረት ያደረገ የመፍትሔ ሀሳብ ማመንጨት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ፎረሙ በማኅበረሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። እየሠሯቸው ባሏቸው ሥራዎች ለውጥ እያዩ መኾኑንም ገልጸዋል። ካለው ችግር አንጻር ግን የተሠራው ሥራ አሁንም በቂ አይደለም ነው ያሉት።
መፍትሔው ዝምታ አይደለም ያሉት ጸሐፊው ፎረሙ ገለልተኛ ነው፣ ሚዛናችን ይዘን እንቀጥላለን፣ ማዕከል የምናደርገው ማኅበረሰቡን ነው፣ ገለልተኛ ኾነን ስትራቴጂ ሰነዶችን እናዘጋጃለን ብለዋል። መውጫ መንገድ የምንለውንም የመፍትሔ ሀሳብ እናመለክታለን ነው ያሉት።
በተፈጠረው ግጭት የአዕምሮ ጤና እና የሥነ ልቦና ጫና እየደረሰባቸው ያሉ ወገኖች ነገ ተስፋ ያላቸው እና ለሀገር የሚጠቅሙ መኾናቸውን ገልጸዋል። በሥነ ልቦና ጠንካራ እንዲኾኑ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። በዚህ ወቅት አንድ መኾን እና በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ምሁራን ገለልተኛ ኾነው በሙያቸው መፍትሔ ማበጀት አለባቸው ነው ያሉት። ሁሉም ሰው በሙያው አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባውም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!