“ዋናው ነገር …ጤና”

28

ባሕር ዳር: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‘ዋናው ነገር ጤና’ ተብሎ የተዜመለት ነው የሰው ልጅ ጤና። ትናንትን ዞር ብሎ ለማየት እና ለኾነልን፣ ለተደረገልን ሁሉ ለማመሥገን፣ ዛሬን ለመኖር እና ነገንም ለማለም ዋናው ነገር ጤና ነው። እናም ለጤና ‘ዋናው ነገር ጤና’ ተብሎ ቢዜምለት ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም።

መንግሥትም ከዜማው ባሻገር ስለጤና የተረዳ ይመስላል። የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅንን በአዋጅ ቁጥር 6/2002 ደንግጓል። ለምን ቢሉ የጤና አገልግሎት መስፋፋት ለሀገሪቱ የተቀላጠፈ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉልህ ድርሻ ያለው በመኾኑ።

ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ በመንግሥት እና በተጠቃሚው ኅብረተሰብ መካከል ወጭን መጋራት ወሳኝ ኾኖ በመገኘቱ እና በአባላት መካከል መደጋገፍን በመፍጠር ፍትሐዊ እና የተሻለ የጤና አገልግሎትን ለማጎልበት የሚረዳ ቀጣይነት ያለው የጤና ፋይናንስ ማሠባሠቢያ ስልት በመኾኑ ነው።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረትም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት ዓላማ ተጠቃሚው በጤና ተቋማት አገልግሎት በሚሻበት ወቅት አብዛኛውን ከኪስ የሚከፈል ወጭ በመቀነስ ጥራት ያለው እና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያገኝ ማስቻል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር በ2012 በነበረው 67ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ተወያይቶ ባጸደቀው ዓለም አቀፍ የጤና እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይም ትኩረት ከሰጣቸው ርዕሶች ዋነኛው ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ነው፡፡ በዚህም ጉባኤ ላይ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለጤና ከኪስ በሚያወጡት ክፍያ ምክንያት ወደ ድህነት እየገቡ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ ይህን ከፍተኛ ወጭ በመፍራትም የጤና አገልግሎትን ከማግኘት እያስቀራቸው መኾኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

በጉባኤው ላይም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ከተሰጠው የቤት ሥራ አንዱ በአገልግሎት ማግኛ ቦታዎች የሚደረግን የቀጥታ ክፍያ ለማስቀረት የሚያገለግል የቅድመ ክፍያ ሥርዓት እንዲዘረጋ እና የሕክምና ወጭ ጫናን ዜጎቻቸው እንዲካፈሉ የማድረግ ስልቶችን እንዲነድፉ ነው፡፡

ኢትዮጵያም እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተቀበለች በመኾኑ ይህን ኀላፊነት ለመወጣት ነው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አዋጅን በምክር ቤት አጸድቃ ወደ ተግባር የገባችው፡፡ መንግሥት ከሕዝብ በሚሠበሥበው የታክስ ክፍያ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መገንባት እና ጥቂት የማይባሉ የጤና አገልግሎቶችን ከክፍያ ነጻ በኾነ መልኩ እያቀረበ ቢኾንም የሁሉንም ዜጋ የጤና አገልግሎት ፍላጎት ከክፍያ ነጻ ለማድረግ ግን አቅሙ አይፈቅድም፡፡ ዜጎች አስቀድመው በሚያዋጡት የተወሰነ መዋጮ የጤና አገልግሎትን ከፍለው እንዲጠቀሙ ማድረግን አማራጭ አድርጓል፡፡

በመኾኑም የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርዓት አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ የጤና አገልግሎት ወጭ የሚሸፈንበት ሥርዓት ሲኾን የከፍተኛ የጤና ወጭ ስጋትን በመቅረፍ እና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ሁሉም እንደህመሙ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾን የሚያስችል ነው፡፡

ኅብረተሰቡ የሚያዋጣውን አነስተኛ መዋጮ በአንድ ቋት በማሠባሠብ የእርስ በእርስ የመደጋገፍ ባሕልን በማጎልበት ጤነኛው ታማሚውን፣ የተሻለ ገቢ ያለው አነስተኛ ገቢ ያለውን እንዲሁም ወጣቱ አዛውንቱን የሚደጉሙበት ነው፡፡

ስለኾነም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የጥቅም ማዕቀፍ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በአዋጅ ቁጥር 1273/2014 መሠረት የምዝገባ ወቅት በተመረጡ በየዓመቱ ሁለት ወራት ብቻ የአባላት ክፍያ በመክፈል አገልግሎታቸውን ያሳድሳሉ፤ አዲስ አባላት ደግሞ ምዝገባ ያካሂዳሉ።

የጤና መድኅን አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ኢ-መደበኛ በኾኑ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሲኾን በሀገሪቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ላይ እንደተገለጸው በ2030 ዓ.ም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ ዓላማ ተደርጓል፡፡

ዘጋቢ፡- ደመወዝ የቆየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከውጭ ይገባ የነበረውን ማዕድን በሀገር ውስጥ በመተካት ከ102 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳን ተችሏል” የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ
Next article“በማኅበረሰቡ እየደረሰ ላለው የሥነ አዕምሮ ጤና እና የሥነ ልቦና ችግር ትኩረት ማድረግ ይገባል” ታፈረ መላኩ (ዶ.ር)