
ባሕር ዳር: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ10 ዓመቱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅዶች ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው እና የሀገሪቱን ልማት ያጠናክራሉ ተብለው ከተቀመጡ አምስት ዘርፎች መካከል የማዕድን ሃብት አንዱ ነው።
ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ ክልሉ ካለው 181 ሺህ 190 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ውስጥ በ45 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ 45 ማዕድናት መለየት መቻሉን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታምራት ደምሴ ገልጸውልናል።
በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪው ግማሽ ዓመት ከማዕድን ሃብት ለመሠብሠብ ከታቀደው 101 ሚሊዮን ብር በስድስት ወራት 33 ሚሊዮን ብር ተሠብስቧል ነው ያሉት።
ከውጭ ይገባ የነበረውን ማዕድንም በሀገር ውስጥ በመተካት ከ102 ሚሊዮን በላይ ዶላር ማዳን መቻሉን ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት። ከውጭ ይገቡ ከነበሩት ማዕድናት ውስጥ ደግሞ ግራናይት አንዱ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ ማዕድናትን ማምረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ የመላክ ችግር መኖሩንም ገልጸዋል።
በቀጣይ ለባለሙያዎች እና ጌጣጌጥ ላይ ለተሠማሩ ወጣቶች ሥልጠናዎችን ማጠናከር፣ እሴት መጨመር የሚያስችሉ ግብዕቶችን ማጠናከር ትኩረት የተሠጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!