
አዲስ አበባ: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም የኢንቨስትመንት ፓስፖርት ነው” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ኤክስፖ ሊካሄድ መኾኑ ተገልጿል፡፡ የኢንዱስትሪ ከተማ በኾነችው ኮሞቦልቻ ከተማ ከሚያዚያ 20/2017 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 29/2017 ዓ.ም ድረስ ነው የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ኤክስፖ የሚካሄደው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት አንዱ አካል የኾነው የኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ እና ፋይናንስ ኤክስፖ 2017 በተለይም የኢንዱስትሪ ከተማዋን ኮምቦልቻን የበለጠ ለማልማት እና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳለው ተነግሯል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ ሚያዝያ/2017 ዓ.ም የሚካሄደው ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ እና ፋይናንስ ኤክስፖ ዋና ዓላማ ለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ባለሃብቶችን ለመሳብ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው የአካባቢውን ፀጋ ለማስተዋወቅ እና ያለውን አምራች የሰው ኃይል ወደ ሥራ ለማስገባት ኤክስፖው እንደሚያግዝ ነው በሰጡት መግለጫ የተናገሩት፡፡ ኤክስፖው ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ያሏቸውን አዳዲስ ምርቶች እንዲያስተዋውቁ እና ትስስር እንዲፈጥሩ ለማድረግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል፡፡
በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ እና ፋይናንስ ኤክስፖ ላይ ከ300 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስተሮች፣ 50 የሚኾኑ የፋይናንስ ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ ከ30 በላይ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ከ20 ያላነሱ ሥራ ፈጣሪዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ኤክስፖ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገበት እንደኾነ የተናገሩት ምክትል ከንቲባው በተለይ ማኅበረሰቡ ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ ከፍያለ መኾኑ ሀገር አቀፍም ኾነ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ እና ፋይናንስ ኤክስፖ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ብሎም የልማቱ አጋር እንዲኾኑ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!