
ደብረ ብርሃን: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐግብር ተጠቃሚ የኾኑ የቤተሰብ መሪዎች ተመርቀዋል፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐግብርን በመተግበር በኅብረተሰቡ ውስጥ የግል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመርሐግብሩ ግለሰባዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር በከተማ ጽዳት፣ ውበት እና በአረንጎዴ ልማት በስፋት እየተሠራ ይገኛል፡፡
በዚህ መርሐግብሩ ከሦስት ዓመት በፊት ተጠቃሚ የኾኑ 442 የቤተሰብ መሪዎች ዛሬ ተመርቀዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚ የኾኑ ወገኖች ከጊዜያዊ እገዛ ባለፈ በኑሯቸው ላይ መሠረታዊ ልዩነት እንዲፈጥሩ በቅርበት ድጋፍ ሲደረግላቸው ነበር ብለዋል፡፡ መርሐግብሩ የራስን ችግር በራስ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ልምምድ መኾኑንም አንስተዋል ፡፡
የከተማ ልማትን በማፋጠን ረገድ መርሐግብሩ ድርሻው ከፍ ያለ እንደነበር ያኑሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በከተማዋ ጽዳትን ለመጠበቅ እና በአረንጎዴ ልማት ዘርፍ የተደረገው ጥረት ማሳያ መኾኑን፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ የምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ ድባቤ በዚህ መርሐግብር የታቀፉትን ወገኖች ከተረጅነት በማላቀቅ ጥሪት እንዲፈጥሩ ያገዘ ነው ብለዋል፡፡
አባላቱ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ማግኘታቸውን የተናገሩት ኀላፊው የራሳቸውን ገቢ በማሳደግ የቁጠባ ባሕልን እንዲያዳብሩ ተደርጎል ነው ያሉት፡፡ በመርሐግብሩ ከ37 ሺህ በላይ በከተማዋ የሚገኙ ነዋሪዎች ታቅፈዋል። ከዚህ ውስጥ ከ20ሺህ በላይ የሚኾኑት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ወገኖች ናቸው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በዚህ መርሐግብር ታቅፈው ዛሬ የተመረቁትን ወገኖች በዘላቂነት ለማጠናከር ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ በዚህ መርሐግብር በአዲስ የታቀፉትን ከ8ሺህ 700 በላይ ወገኖችን ውጤታማ በኾነ መንገድ ለመደገፍም እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ገንዘብ ታደሰ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!