አካታችነትን መርህ አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

25

ባሕር ዳር: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመቋቋሚያ አዋጁ 1265/2014 አካታችነትን የሀገራዊ ምክክሩ የመጀመሪያ መርህ አድርጎ ደንግጓል፡፡ ኮሚሽኑ ለዘለቄታው የሚበጁ ሀገራዊ የመፍትሄ ሀሳቦችን አካታች በኾነ መንገድ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት እና ዲያስፓራው ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እስከወረዳ ድረስ በማሳተፍ የሕዝብ ሀሳቦች በአግባቡ በአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደቶች እንዲወከሉ አድርጓል ነው የተባለው፡፡ ያንን ተከትሎም ልዩ ልዩ ተቋማትን እና ማኅበራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማሳተፍ አጀንዳዎችን በ10 ክልሎች እና ሁለት የከተማ አሥተዳደሮች ማሠባሠብ ችሏል፡፡

በቀጣይም ኮሚሽኑ በፌዴራል ደረጃ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ አጀንዳን እንደሚሠበሥብ ይጠበቃል፡፡ ኮሚሽኑ በዚህ የአካታችነት አውድ ውስጥ ሲሠራ ነፍጥ አንግበው በጫካ የሚገኙትን ወገኖች ጨምሮ በሀገር ጉዳይ ላይ ይመለከተናል ለሚሉ አካላት በሙሉ የአብረን እንሥራ ጥሪንም አቅርቦ እየሠራ ይገኛል፡፡

ችግር አለብን የሚሉትንም ያለምንም የደኅንነት ስጋት ወደ ጠረጴዛ በመምጣት ስለሀገር የሚመክሩበትን ሂደትም ሲያመቻች ቆይቷል፤ እያመቻቸም ይገኛል፡፡ ኮሚሽኑ አካታችነትን የቁጥር ወይንም የኮታ ጉዳይ ብቻ አድርጎ ሳይመለከት የሀሳብ ብዝኅነት የሚስተዋልበትን ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ የድርሻውን እየተወጣም ይገኛል፡፡

ለአብነትም ኮሚሽኑ በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች በምክክር ሂደቱ ተሳትፈው ሀሳባቸውን እንዲያሰሙ ጥሪውን አቅርቦ የብዙዎችን አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ ነው የተገለጸው፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደትን ባከናወነባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አበረታች ሥራዎች የተከናወኑ ሲኾን ባለድርሻ አካላትም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን በነፃነት አሰናድተው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸው ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህም በኋላ በሚያከናውናቸው የምክክር ሂደቶች ከማንኛውም የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች ጋር በጋራ ለመሥራት አሁንም በሩ ክፍት መኾኑን ነው የገለጸው፡፡

ሰላምን ለማስፈን እና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት በሀገር አንድነት ውስጥ ለመገንባት እና ለማስጠበቅ፣ ሀገር አቀፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ነው ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያብራራው፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን ብሔራዊ ኮሚቴው አስታወቀ።
Next articleበደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሪደር ልማት በሰባት ከተማ አሥተዳደሮች ተጀምሯል።