የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን ብሔራዊ ኮሚቴው አስታወቀ።

40

አዲስ አበባ: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማካሄድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ 35 መሥሪያ ቤቶች የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል። የኅብረቱ 38ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ይካሄዳል። 46ኛው የአሥፈፃሚዎች ሥብሠባ ደግሞ የካቲት 5/2017 ዓ.ም እና የካቲት 6/2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

የመሪዎች ጉባኤ ስኬታማ ኾኖ እንዲካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል። ይህ ጉባኤ አዲስ አበባን የኅብረቱ ማዕከልነት ለማፅናት ጠቃሚ በመኾኑ እና ለሱ በሚመጥን መልኩ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። ኢትዮጵያ እንደአዘጋጅ ሀገር ምን እንደሚጠበቅባት በ3 ቋንቋዎች የዝግጅት ፕሮቶኮል ማኑዋል ማዘጋጀቷንም አንስተዋል።

እንግዶች ከቪዛ፣ ከቋንቋ እና ከአንቅስቃሴ አንጻር ችግር እንዳይገጥማቸው በየዘርፉ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

የተለያየ ቋንቋ የሚችሉ 101 በጎ ፈቃደኛ ፕሮቶኮል ካዴት፣ 97 መደበኛ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ በጸጥታ፣ በሆቴል፣ በኢምግሬሽን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በመዝናኛ ስፍራዎች ዝግጅቶቹ ተጠናቅቀዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተቋማት በቅንጅት በመሥራት የሕዝብን ችግር መፍታት አለባቸው” የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ
Next articleአካታችነትን መርህ አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡