“ተቋማት በቅንጅት በመሥራት የሕዝብን ችግር መፍታት አለባቸው” የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ

56

ባሕር ዳር: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ተቋማት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው እና ሁሉም የዘርፉ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ መልእክት ያስተላለፉት አቶ ደሳለኝ ጣሰው የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ተቋማት አመራሮች እና አጠቃላይ የሥራ አባላት በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ የታቀዱ የልማት ሥራዎችም እንዲፈጸሙ ለማስቻል ሲተጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በተለይም የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ እና የተጋረጠበትን አደጋ ለመቀልበስ አስፈላጊውን ሁሉ መስዕዋትነት ለመክፈል የተዘጋጁ ተቋማትን የያዘ ዘርፍ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

አቶ ደሳለኝ በክልሉ ሰላም እና መልካም አሥተዳደርን ለማስፈን ሲሉ ዋጋ ሲከፍሉ ለቆዩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል። የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ተቋማት ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ እና በሕዝባችን ላይ የሚደርስ ሰቆቃ እና ምሬትን ቅርብ ኾነው የሚፈቱ ናቸው ብለዋል። በመኾኑም በሁሉም ተቋማት ልዩ የትኩረት አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ነው ያሉት።

እንደ ክልል የተፈጠረውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት የአቅም ግንባታ እና የመፈጸም ብቃትን ማሳደግ ዋነኛ ተግባር እንደ ነበርም ተናግረዋል። ሕዝብን ለማገልገል የተዘረጉ ተቋማትን የሚመሩ አካላትን የመፈጸም አቅም በማብቃት አገልጋይነትን ከፍ ማድረግም የትኩረት አቅጣጫ ነበርም ብለዋል።
የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በቁርጠኝነት በማከናወን ሕዝብ የሚተማመንበት ተቋም ለመገንባትም ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።

በቀጣይም ሕዝብን የሚያማርሩ አገልግሎት አሰጣጦችን በማረም፣ አገልጋይነትን የበለጠ በማሳደግ እና የሕዝብን እርካታ በማሳደግ ሕዝብ የሚተማመንባቸው ተቋማትን መፍጠር ግድ እንደሚል አሳስበዋል። በሁሉም ተቋማት አዳዲስ ለውጦችን መተግበር እንደሚገባም አሳስበዋል። የሚፈጠሩ ለውጦች ከቆዩ ችግሮች የሚያላቅቁ፣ ዘመኑን የዋጁ፣ ፈጣን እና ሕዝብን ለማገልገል የተመቹ መኾን አለባቸው ብለዋል።

ተቋማት የተሻለ ለውጥ ያመጡ ዘንድ የተሻለ ቅንጅታዊ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም አቶ ደሳለኝ ጠቁመዋል። ለሕዝቡ ተደራሽ የኾነ የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት ጠንካራ የፖሊስ ተቋም መገንባት እና የምርመራ አቅምን ማሳደግ ይጠይቃል፤ ለዚህም በትብብር መሥራት ግድ ይላል ነው ያሉት።
“የተቀበልነው ሕዝባዊ ኀላፊነት ትልቅ መኾኑን በመረዳት አንዱ ተቋም ከሌላው ተቋም በመቀናጀት የሕዝብን ችግር መፍታት መቻል አለብን” ሲሉም አሳስበዋል።

በዛሬው የግምገማ እና ውይይት መድረክ ላይ በአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ተቋማት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን አቅርበው ያስገመግማሉ። ከውይይቶች በኋላም ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ተጠቁሟል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ወጣቶች ለተሐድሶ ሥልጠና ወደ ጠዳ የሥልጠና ማዕከል ገቡ።
Next articleየአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን ብሔራዊ ኮሚቴው አስታወቀ።