
ከሚሴ: የካቲት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ከፍ ያለ ቋት ጉባኤ ምስረታ በከሚሴ ከተማ አካሂዷል። በጉባኤ ምስረታው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን በጤናው ዘርፍ ውጤታማ የለውጥ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በተለይም የጤና ተደራሽነት እና ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡አካታች እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳካት ከተቀረጹ ሪፎርሞች መካከል አንዱ የጤና መድኅን ሥርዓት መኾኑን ምክትል ቢሮ ኀላፊው አብራርተዋል። ይህም ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘ መኾኑን አቶ ገስጥ ጥላሁን አመላክተዋል። የጉባኤ ምስረታው የጎንዮሽ መደጋገፍ ሥርዓትን በመዘርጋት የስጋት ተጋላጭነትን መቀነስ ብሎም የተቋማቱን ኪሳራ በማስወገድ የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነውም ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የጤና መድኅን ሥርዓት ዓላማ ዜጎች አስቀድመው በሚከፍሉት መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ያለምንም የክፍያ ስጋት የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል መኾኑን ተናግረዋል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ ኡስማን አሊ የጉባኤው መመሥረት የተሻለ የሀብት አሠባሠብ ሥርዓትን በመፍጠር አባላቱ ምቹ እና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል። ኀላፊው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የዞን ቋት ማቋቋም እና ገቢን መሠረት ያደረገ የመዋጮ አከፋፈል ሥርዓት የገንዘብ ችግር ሳይገጥማቸው አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት በፍትሐዊነት እንዲያገኙ የሚያስችል መኾኑን ጠቁመዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች በዞን ደረጃ አንድ ቋት መዘጋጀቱ የሀብት ብክነትን ከመከላከል ባሻገር ወረዳዎች እረስ በእርስ እንዲደጋገፉ የሚያደርግ መኾኑን አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!