
አዲስ አበባ: የካቲት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሐምሌ/2016 ዓ.ም ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ሥራ አሥፈጻሚ ቦርድ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን መደገፍ የሚያስችል ለኢትዮጵያ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት ማጽደቁ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው ያለውን ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የትግበራ አፈጻጸም በሚመለከት የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ለመገናኛ ብዙኅን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአይ ኤም ኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በገበያ ላይ የተመሠረተው የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት ትግበራ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ማድነቃቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ሀገሪቱ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እና በገበያ ላይ የተመሠረተው የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት ትግበራ በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት እንዳስቻለ አንስተዋል። በገበያ ላይ የተመሠረተው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ቀደም ሲል በሀገሪቱ ይስተዋል የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ማስቻሉን ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ በተለይም የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና በማረጋጋት፣ የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ፣ የግል እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የፋይናንስ አቅም በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም ሀገሪቱ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአይሲቲ እና በሌሎች ዘርፎች ተወዳዳሪ ለመኾን እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት አስችሏታል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
አይ ኤም ኤፍ፣ የዓለም ባንክ እና ሌሎች ደጋፊ የልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ የመንግሥት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መኾኑን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!