
ደባርቅ: የካቲት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል የስድስት ወራት የትምህርት አፈፃፀም ግምገማ በደባርቅ ከተማ አካሂዷል። በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክቡር አሰፋ፣ በዞኑ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል 79 በመቶ የሚኾኑት ብቻ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ከ250ሺህ በላይ ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ ከ170ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገብ መቻሉንም አስታውሰዋል።
የመማሪያ መጻሕፍት እጥረቶችን ለመፍታት እና አንድ ለአንድ ለማዳረስ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በትብብር እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል። የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን በትምህርት ዝግጅት ለመደገፍ ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙም አቶ ክቡር አንስተዋል። ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ እና የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አቶ ክቡር ጠይቀዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን መምህራን ማኅበር ሊቀመንበር መምህር ሀብታሙ አቸነፍ “የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይደናቀፍ እና ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ መምህራን በአስቸጋሪ ኺኔታዎች ውስጥ እያለፉም ቢኾን ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው” ብለዋል።
የመማሪያ መጽሐፍት እና የአጋዥ መጽሐፍት እጥረት፣ የቤተ-ሙከራ እና የቤተ-መጽሐፍት አለመሟላት እና የጸጥታ ችግሮች በተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸውን ገልጸዋል።
ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን በሥነ-ልቦና እና በትምህርት ዝግጅት መደገፍ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚኾን ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!