
ባሕር ዳር: የካቲት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት መሪዎች የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ እንዲያገኙ ያሳዩት ቁርጠኝነትና አጋርነት ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (EAC) እና የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (SADC) በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የጋራ የመሪዎች ስብሰባ በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ተካሄዷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በስብሰባው የተገኙ ውጤቶች እና ውሳኔዎችን በመልካም ጎኑ እንደምታያቸው ገልጿል።
ኢትዮጵያ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን (ዶ.ር)፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት እና የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ሊቀመንበር ዊሊያም ሩቶ (ዶ.ር) እና የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት እና የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ ሊቀመንበር ኤመርሰን ምናንጋግዋ ስብሰባው በስኬት እንዲጠናቀቅ ያሳዩትን አመራር አድንቃለች።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የማበጀት መንፈስ ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ያሳዩት ትብብር እና ቁርጠኝነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ተግባር እንደኾነ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!