
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በጎንደር አዘዞ ጠዳ የተሀድሶ ሥልጠና ሲወስዱ ቆይተው ለተመለሱ ሠልጣኞች የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር አቀባበል አድርጓል። ሥልጠናውን ወስደው ከተመለሱ ሠልጣኖች መካከል አቶ ጌትነት አስፋው ሲሄዱበት የቆዩት የተሳሳተ መንገድ የእርስ በእርስ መጠፋፋት ከማምጣት ውጭ የአማራን ጥያቄዎች የሚመልስ አለመኾኑን በመረዳት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሥልጠና መግባታቸውን ነግረውናል።
በሥልጠናው የሀገርን እና የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ጥሩ ግንዛቤ የጨበጡበት እንደነበርም አስረድተዋል። ሌላኛው ሠልጣኝ አቶ መለሰ ዳኘ ሢሠሩት የቆዩት ተግባር የተሳሳተ መኾኑን ተረድተው የመንግሥትን ጥሪ መቀበላቸውን ነው የተናገሩት። በተሃድሶ ሥልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ በመጠቀም ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት። ሌሎች ሥልጠናውን ወስደው የተመለሱ ወጣቶችም የእርስ በእርስ መጠፋፋት እንዲቆም እና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ያልተቀበሉ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አበባው በለጠ ሥልጠናውን ወስደው የተመለሱ ወጣቶች ከቀደመ ስህተታቸው ተምረው ለማኅበረሰባቸው አርዓያ በመኾን ወደ ቀደመ ሥራቸው ተመልሰው ሕይዎታቸውን እንዲመሩ ይደረጋል ብለዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የኔነህ ሁነኛው ወጣቶቹ የሰላም አምባሳደር በመኾን የበደሉትን ሕዝብ መካስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በሚሄዱበት ወረዳም በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተሳታፊ በመኾን የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!