የጠረጴዛ እርከን ልማቱ ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ እንደሚሆን ርእሰ መሥተዳድሩ ገለጹ።

217

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እየተከናወነ ያለውን ውጤታማ የጠረጴዛ እርከን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሠራ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ተናገሩ።

ርእሰ መስተዳድሩ በደቡብ ወሎ ዞን የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ የተፋሰስ ልማትን ጎብኝተዋል።
በብሔረሰቡ ልዩ ወረዳው 9ኙም ቀበሌዎች የተፈጥሮ ሀብት የተፋሰስ ልማት እንደሚከናወን የብሔረሰብ ልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሙሃመድ የሱፍ ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው 22 የተፋሰስ ልማቶች ተለይተው በጠረጴዛ እርከን አቮካዶ፣ ማንጎና ሀብሀብ የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት።

አርሶ አደር አህመድ ሰይድ በብሔረሰብ ልዩ ወረዳው 01ቀበሌ በተከናወነው የጠረጴዛ እርከን የተፋሰስ ልማት አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ ተጠቃሚ እየሆኑ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት የተፋሰስ ልማት ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ወጣቶች ወደ ስደት ከመሄድ ተቆጥበው እየተደራጁ በአካባቢ ጸጋ እየተጠቀሙ መሆኑን ነግረውናል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ታደሰ ግርማ እንዳሉት የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ልማትን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል የተከናወነው ተግባር አበረታች ውጤት አስመዝግቧል።

በተያዘው ዓመትም ከ16 ሺህ በላይ ወጣቶችን በግብርና ልማት ዘርፍ ለመፍጠር ታልሞ እየተሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው በአርጎባ ማኅበረሰብ እየተከናወነ ያለው የጠረጴዛ እርከን የተፋሰስ ልማት ሥራ ለሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል። ይህን መልካም ተሞክሮ በማስፋት የክልሉን አርሶ አደር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም ነው ያረጋገጡት።

የተፈጥሮ ሀብት የተፋሰስ ልማት ሥራውን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በማስተሳሰር የገጠር ወጣቶች ሀብት እንዲያፈሩም በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው እሸቴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዮቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleፍርድ ቤቱ በእነ አቶ በረከት ስምዖን የክስ መዝገብ የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ለሚያዝያ 30 ቀጠረ፡፡
Next articleከ43 ሺህ በላይ ሰዎች የሰውነት ሙቀት ልኬታ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡