ሳምንቱ በታሪክ

90

አቤ ጉበኛ ሲታዎስ!
ባሕር ዳር: የካቲት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደራሲ አቤ ጉበኛ በአማራ ክልል ጎጃም አቸፈር ወረዳ ልዩ ስሙ ኮረንች አቦ በተባለ ቀበሌ በ1925 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡
ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በመጀመሪያ የአብነት ትምህርቱን በይስማላ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዜማውን፣ ዳዊቱን፣ ቅኔውን እና አቋቋሙን ለ12 ዓመታት የተከታተለ ሊቅ ነበር፡፡ ቅኔ አዘራረፋቸውንም ሰምቶ አቃንቶ ሲያስተካክል መምህሩ “እሱ አቤ ጉበኛ ሳይሆን አቤ ጉደኛ ነው” ብለውታል፡፡

አቤ ከሃይማኖታዊ ትምህርት በተጨማሪ የዘመናዊ ትምህርቱን በዳንግላ ከተማ ሲከታተል ቆይቶ በ1946 ዓ.ም ዳንግላን ትቶ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ባዕታ ቤተ ክርስቲያን ተጠግቶ እንደ ቆሎ ተማሪ ኾኖ ቆይቷል፡፡
አቤ የቤተክርስቲያን ሊቅ ስለነበር አዲስ አበባ ሀና ማርያም በመርጌትነት ተቀጥሮ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን እና መዘምራንን ይመራ ነበር፡፡

ገና ዳንግላ ዘመናዊ ትምህርት በመማር ላይ እያለ የጀመረውን የአማርኛ ግጥም የመፃፍ ፍቅሩን በማጠናከር በ24 ዓመቱ ሚያዚያ 12/1949 ዓ.ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ልቡ ገበሬው ዘንድ መሆኑን የሚያመለክት በኅብር መንገድ አንድነት ያለውን ጠቀሜታ በግጥሙ በመግለጽ በጋዜጣው እንዲወጣ አድርጓል፡፡

በዚሁ ጋዜጣ ግንቦት 10/1949 ዓ.ም “የሀዘን እንጉርጉሮ” በሚል የፃፈው ግጥሙ በውስጡ ያመቀውን ከመተንፈስ ወደ ኋላ የማይል ደራሲ መኾኑን አመላክቷል፡፡ በ1949 ዓ.ም መጨረሻም “ከመቅስፈት ሰራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት” በሚል ርዕስ አነስተኛ የግጥም መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ይህንን ክህሎቱን በማየትም በ1951 ዓ.ም በ26 ዓመቱ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ተቀጥሮ ሠርቷል፡፡ ብልሹ አሠራሮችን በመቃወም ይጽፍ እንደነበር የአቤ ጉበኛ የሕይወት ታሪክ ያስረዳል።

አቤ በ1956 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ “ሰይፈ ነበልባል” የተሰኘውን መጽሐፉንም አሳትሟል፡፡ እንደ አልወለድም እና መሰል የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹን በማሳተም ለሕዝብ አሳቢነቱን አሳይቷል። አቤ በሕይወት ዘመኑ ከ27 በላይ መጽሐፍቶችን የፃፈ ሲኾን ከእነዚህም መካከል ከመቅፅፍት ሠራዊት ይጠንቀቅ፣ የሮም አወዳደቅ፣ ቂመኛው ባህታዊ፣ የአመፅ ኑዛዜ፣ አልወለድም፣ የፍጡራን ኑሮ፣ ዘ ሳቬንጅ ገርል፣ የራሄል እንባ፣ ሰይፈ ነበልባል፣ አንድ ለእናቱ፣ መስኮት፣ ዕድል ነው በደል፣ የሀሜት ሱሰኞች፣ ጎብላንድ፣ አጭበርባሪው ጦጣ፣ የሕይወት ተርጓሚዎች፣ የረገፉ አበቦች፣ እሬት እና ማር፣ የደካች ወጥመድ፣ መሬት የማነው፣ ዲፌንስ፣ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ተጠቃሽ ናቸው። የበርካታ ድርሰቶች ባለቤት አቤ ጉበኛ በነበረው አቋም የካቲት 01/19 72 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ሕይዎቱ ሊያልፍ ችሏል።

👉የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምሥረታ
በዚህ ሳምንት ጥር 29/1953 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንጻ ታንጾ ተመረቀ። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ለዕይታ የበቃውና ባማረ መልኩ ምርቃቱን ለማብሰር የተቀረጸው የንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መልዕክት ‹‹ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ሕዝብ የወደፊት ዕድገት መታሰቢያ ይኾን ዘንድ ከሀሳባቸው አንቅተው መርቀው የመሰረቱትን ይህን ሕንጻ ጥር 29/1953 ዓ.ም የአፍሪካ አዳራሽ ብለው ሰየሙት” ይላሉ።
በርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች የሚከወኑበት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (በእንግሊዘኛ ምሕጻረ ቃል ኢ.ሲ.ኤ የሚባለው) ሕንፃ የተመረቀው በዚህ ሳምንት ነበር።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በ1950 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ተፈርሞበታል። በመሐል አዲስ አበባ ካዛንቺስ የሚገኘው ይህ ሕንጻ በስድስት ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባ ስለሠኾኑም ታሪኩ ያስረዳል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት የሚገኝበት ሕንጻ 55 ሺህ ካሬ ቦታ ላይ ያረፈ ነው። የተሠራውም የአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ሊመከርበት ታስቦ ነው። በዚህም መሠረት የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሦስተኛውን ጠቅላላ ሥብሠባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደው በዚሁ አዳራሽም ነበር።

ቤተ መጻሕፍት እና ሌሎች ሰፋፊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ያሉት ይህ ግዙፍ ሕንጻ፤ የአርክቴክት ባለሙያውም ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ኢንጂነር ጌታቸው ማህተመሥላሴ ይባላሉ።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የሊቀመንበር 8፣ የአማካሪዎች 36፣ የተመልካች 48፣ የአስተርጓሚ 8፣ የጋዜጠኞች 225፣ የልዩ እንግዳ 37 ወንበሮች እንዲኖሩት ተደርጎ ነበር የተሠራው።

👉የቦብማርሌ ልደት!!
ቦብ ማርሌ በአጭር ሕይዎቱ የምርጥ የሬጌ ዘፋኝን ማዕረግ ማግኘት የቻለ ሙዚቀኛ ነው። ኢትዮጵያን አጥብቆ እንደሚዎድ የሚነገርለት ሮበርት ኔስታ ማርሌይ በዚህ ሳምንት ጥር 29/1937 ዓ.ም ጃማይካዊ የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ፣ ቦብ ማርሌ ተወለደ። አባቱ ወታደር ነበር እናቱ ደግሞ ለረጅም ጊዜ የቤት እመቤት እንደነበረች ነው የሚነገረው። ቦብ ወደ ትምህርት ከተቀላቀለ በኋላ በመርህ ደረጃ ወደ ሳይንስ ዕውቀት አልተሳበም ይሉታል።

ይሁን እንጅ ሙዚቀኛው ከጃማይካ የሙዚቃ ስልተምቶች አንዱ በኾነው ስካ ዳንስ ዘልቆ በመግባት የፈጠራ ችሎታውን ማሳየት ጀመረ። ቦብ ማርሌ በሙዚቃ ውስጥ በንቃት መሳተፍም ጀመረ። ቦብማርሌ የመጀመሪያውን የሙዚቃ ሙከራ በራሱ ማድረግ እንደጀመረ ነው የሚነገረው። ቦምባርሌ ዘዋኢለርስ (“The Wailers”) የተባለውን ቡድን ካቋቋመ በኋላ ግን የተሻለ እንደኾነለት ነው ታሪኩ የሚያስረዳው።

የቦብ ማርሌ ተወዳጅነት ጫፍ የጀመረው “ዋኢለርስ” በተባለው የሙዚቃ ቡድን እንደኾነ ነው ብዙዎች የሚስማሙት። ይህ የሙዚቃ ቡድን ሙዚቀኛውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እና ዝና አምጥቶለታል። ቦብ ማርሌ በሙዚቃ ሕይዎቱ መጀመሪያ ላይ ነጠላ ዘፈኖችን እና አልበሞችን እንደ ቡድን ቀርጿል። ትንሽ ቆይቶ፣ ቡድኑን ወደ ራሱ በመለወጥ፣ ዘ ዋኢይለር እና ቦብ ማርሌ በሚል ሲንቀሳቀስም ቆይቷል።

“ዋኢይለርስ እና ቦብ ማርሌ” በአሜሪካ እስያ እና አፍሪካ ውስጥ በጣም ደማቅ ትርዒቶችን በማቅረብም ታሪክ ሁሌም የማይረሳቸው ሥራዎችን ሠርተዋል።
ቦብ ማርሌ ከሙዚቃ በተጨማሪ በስፖርት ዘርፍም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ብዙ ጊዜ ሬጌ ካልኾነለት ሕይዎቱ ወደ እግር ኳስ ይሄድ እንደነበር ነው የሚገለጸው።
ለስፖርቱ ያለው ፍቅር በጣም ትልቅ እንደነበር የሚነገረው ቦምባርሌ ለእግር ኳስ ፍላጎት እንደነበረው ነው ታሪኩ የሚያስረዳው።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመደመር መንገድ ወደ ብልጽግና ግብ ለመድረስ እጅግ የተሻለው መንገድ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article24 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕጢ በቀዶ ጥገና ማስወገዱን እንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል አስታወቀ።