
ባሕር ዳር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ እያካሄዱ ነው። በውይይቱ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ዓላማ በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን ወደ ሁሉም መሪዎች፣ ፈጻሚዎች እና ወደ ሕዝቡ በማውረድ ለመተግበር ያለመ ነው። በተጨማሪም የክልሉ ወቅታዊ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ተነስተው ምክክር ተደርጎባቸዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ካደረጉት ከፍተኛ መሪዎች መካከል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊው ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ ከመጀመሪያው መደበኛ ጉባኤው ወዲህ ትልልቅ ሀገራዊ የልማት ድሎችን አስመዝግቧል ብለዋል።
ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር፣ የሌማት ቱሩፋት ሥራዎችን ለማስፋፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎችን ለማከናወን እና የመስኖ ስንዴን በስፋት በማልማት ከተረጅነት ለመላቀቅ የሚያስችሉ ውሳኔ እና አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህንን ተከትሎም በተለይም በገጠር ልማት ዘርፍ ተጨባጭ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል። በተለይም ስንዴን በስፋት በማምረት በኩል የተቀመጠውን አቅጣጫ በአግባቡ መፈጸም ተችሏል ብለዋል። መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ በተለይም የገጠር መንገድ ተደራሽነት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና አማራጭ የኀይል ምንጭ አቅርቦቶች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ነበሩ ብለዋል። ነባር መንገዶችን የመጠገን እና አዳዲስ መንገዶችን በመገንባት የመንድ አውታሮችን የማሳደግ ሥራም እንደአቅጣጫ ተይዞ እየተሠራበት ነው ብለዋል።
ግብርናን በዘመናዊ የእርሻ ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ለመደገፍም ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት። ከመጀመሪያው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ውሳኔ እና አቅጣጫዎች በመነሳት የግብርናውን ዘርፍ የማሳደግ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፤ በተጨባጭም ዘርፉ እመርታዊ ለውጥ አስመዝግቧል ብለዋል።
በተለይም በ2016/17 የምርት ዘመን በአማራ ክልል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ተሰራጭቷል፤ በዚህም የክልሉን ምርት እና ምርታማነትን ከነበረበት 28 ነጥብ 2 ኩንታል በሄክታር ወደ 32 ነጥብ 3 ኩንታል በሄክታር ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።
169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ 170 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በማግኘት ከዕቅድ በላይ መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት። የተጠናከረ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በማከናወን የክልሉን የደን ሽፋን ወደ 17 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ይህም የመጀመሪያውን የፓርቲው ጉባኤ ውሳኔ እና አቅጣጫዎችን ተቀብሎ በቁርጠኝነት በመተግበር የመጣ ለውጥ ነው ብለዋል።
ለበርካታ ዓመታት ቆመው የነበሩ የመስኖ አውታር ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አሁን ላይ በተፋጠነ ሥራ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ለአብነትም የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን ጠቅሰው ግንባታው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት እንደሚገባ አረጋግጠዋል።
አማራ ክልል ሰፊ የማዕድን ሀብት ያለው ክልል ቢኾንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳይኾን ቆይቷል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዘርፉን ሁነኛ የሀብት ምንጭ እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ ተጨባጭ ለውጦችም ተመዝግበዋል ነው ያሉት። ለአብነትም ግዙፍ የኾነው የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን ጠቅሰዋል። ይህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ የሲሚንቶ ዋጋን በተጨባጭ በማስተካከል የግንባታ ዘርፏንም አነቃቅቷል። በቀጣይነትም ሸበል በረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ እና ሌሎችንም ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑን ዶክተር ድረስ ጠቁመዋል።
የዚህ ሁሉ ስኬት ዋና መነሻው ጉባኤው ያስቀመጣቸውን ውሳኔ እና አቅጣጫዎችን በትክክል ተቀብሎ ወደተግባር ለመተርጎም ጥረት መደረጉ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ ውሳኔ እና አቅጣጫዎችም ያለፉ ዓመታትን ጥንካሬ እና ውስንነት ገምግመው የለዩ፣ ጥንካሬዎችን በማጉላት እና ውስንነቶችን በመቅረፍም ለሀገር ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው ብለዋል።
በመኾኑም የጉባኤውን ውሳኔ እና አቅጣጫዎችን ተገንዝቦ በመተግበር ለበለጠ ሀገራዊ ዕድገት እና የልማት ድል እንረባረባለን ብለዋል ዶክተር ድረስ። ለዚህም ሁሉም ፈጻሚ አካላት እና ሕዝቡ በጋራ ቆሞ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!